ቀጥታ፡

በሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ቤኔፊካ ከሪያል ማድሪድ ሞናኮ ከፒኤስጂ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብር ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል።

በስታዲዮ ዳ ሉዝ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ቤኔፊካ ከሪያል ማድሪድ ይጫወታሉ።



በሻምፒዮንስ ሊጉ አዲስ ፎርማት ቤኔፊካ 24 እና ሪያል ማድሪድ ዘጠነኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በቅርቡ በውድድሩ ላይ አድርገውት በነበረው ጨዋታ ቤኔፊካ 3 ለ 2 አሸንፏል።

ይህም ቤኔፊካን ወደ ጥሎ ማለፍ እንዲገባ ያደረገ ሲሆን፤ ሪያል ማድሪድ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ እንዳይገባ ምክንያት ሆኗል።

ጆዜ ሞውሪኒዮ ቀድመው ያሰለጠኑትን ሪያል ማድሪድ በድጋሚ ይገጥማሉ።



በሌላኛው መርሐ-ግብር ሞናኮ ከፒኤስጂ  በሉዊስ ሁለተኛ ስታዲየም ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ሞናኮ በሊግ እርከን የውድድር ምዕራፍ 21ኛ፣ ፒኤስጂ 11ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ፒኤስጂ የወቅቱ የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ነው።



በሌሎች መርሐ-ግብሮች ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከአትላንታ ምሽት አምስት ሠዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።



ጋላታሳራይ ከጁቬንቱስ ምሽት 2 ሰዓት ከ45  ላይ ይጫወታሉ።

የመልስ ጨዋታዎች በቀጣይ ሳምንት ይደረጋሉ።

በማጣሪያው የሚሳተፉት ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አዲሱ የውድድር ፎርማት ከ9ኛ እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ናቸው።

ከ36 ክለቦች መካከል በስምንት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብተዋል።

አርሰናል፣ ባየር ሙኒክ፣ ሊቨርፑል፣ ባርሴሎና፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ቼልሲ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን በቀጥታ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀሉ ቡድኖች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም