ቀጥታ፡

ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ታሪካዊ አጋርነት 

የኢትዮጵያ እና ቱርኪዬ ግንኙነት ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። የአፍሪካ ጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ኦቶማን ኢምፓየርን ጨምሮ በታሪክ ከመካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ነበራት። ኦቶማን ኢምፓየር ለዘመናዊቷ ቱርክዬ መሰረት ጥሎ አልፏል።

በ20ኛ ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የተጀመረው የሀገራቱ ወዳጅነት በዲፕሎማሲ እና ንግድ ልውውጥ ላይ የተመረኮዘ ነው።

ቱርክዬ አፍሪካን እንደ ስትራቴጂካዊ አጋር የምትቆጥር ሲሆን አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ቁልፍ አህጉራዊ ተቋማት የሚገኙባት እና የአፍሪካ መዲና ኢትዮጵያ የዚህ ትብብር አካል ናት።

ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1896 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የመጀመሪያ የኦቶማን-ቱርክዬ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እ.አ.አ በ1912 በሐረር ከተማ ተከፍቷል።

ቱርክዬ ከሰሃራ በታች የመጀመሪያውን ኤምባሲ የከፈተችው በኢትዮጵያ ሲሆን ወቅቱም እ.አ.አ በ1926 ነበር።

ኢትዮጵያ በቱርክዬ ኤምባሲዋን የከፈተችው እ.አ.አ በ1933 ነው።

ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ግንኙነት ከፍተኛ እድገት ያሳየበት ነው።

ኢኮኖሚ የሁለቱ ሀገራት አጋርነት ምሰሶ እንደሆነ ይጠቀሳል።

የቱርክዬ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በግንባታ እና በግብርና ማቀነባበሪያ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ።

ቱርክዬ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው ሀገራት መካከል በዋናነት ትጠቀሳለች። የሀገራቱ የንግድ ግንኙነትም እየዳበረ መጥቷል።

ከኢኮኖሚ ባሻገር ፖለቲካ፣ ደህንነት፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ እና ባህል ሌሎች የትብብር መስኮች ናቸው።

ባለፉት 10 ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል የከፍተኛ ባለስልጣናት የጉብኝት ልውውጦች ተደርገዋል።

የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን እ.አ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ጉብኝቱ የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትስስር ማጠናከርን ያለመ ነው።

እ.አ.አ በ2017 የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በቱርክዬ ጉብኝት በማድረግ ኢትዮጵያን በመወከል በቱርክዬ-አፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ላይ ተሳትፈዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.አ.አ በ2021 በቱርክዬ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በወቅቱ ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች የትብብር ስምምነቶች መፈራረማቸው ይታወሳል።

ውሃ፣ ወታደራዊ ትብብር እና ፋይናንስ ከስምምነቶቹ ትኩረቶች መካከልም ይገኙበታል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የተደረገው ኢትዮጵያና ቱርክዬ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 125ኛ ዓመት ላይ መሆኑ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት የተፈረሙት ስምምነቶች የግንኙነቱን መጠናከር እንደሚያመለክቱ ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ የልማት እና መረጋጋት ጉዞ ቱርክዬ የምታደርገውን ድጋፍም አድንቀዋል። 

የቱርክዬ መንግስት እና ህዝብ ያደረገልንን የወሳኝ ጊዜ ትብብር ሀገራችን ኢትዮጵያ መቼም አትረሳውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በነበራቸው ቆይታ።

የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እ.ኤ.አ በ2021 በቱርክዬ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በወቅቱ አዲስ የተገነባውን የኢትዮጵያ ኤምባሲም መርቀዋል።

የቱርክዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እ.አ.አ በ2024 ኢትዮጵያን በመጎብኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የከፍተኛ ባለስልጣናቱ ጉብኝት የሀገራቱን የግንኙነት መጠናከር የበለጠ የሚያጎለብቱም ናቸው።

ኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ፣ መሰረተ ልማት፣ የንግድ ብዝሃነትን ማስፋት፣ መከላከያ እና ደህንነት፣ ቱሪዝም እና ባህል ሀገራቱ ትብብራቸውን ሊያሰፉባቸው እየሰሩባቸው ከሚገኙ መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ አጋርነት በጋራ ፍላጎቶች፣ ተራማጅ በሆኑ ሀሳቦች፣ በጋራ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና እየተለወጡ ያሉ የዓለም እውነታዎችን ባማከለ ሁኔታ የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል።

በልማት ጎዳና ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ ከአፍሪካ ጋር ያላት ትስስር የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ ትብብር የበለጠ ጥልቀት የሚሰጥ ነው።

ሁለቱ ሀገራት በፍጥነት እየተለዋወጠ በሚገኘው ቀጣናዊ እና የዓለም ምህዳር ውስጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩም ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም