ኢትዮጵያ በሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ያመጣችው ለውጥ አስደናቂ ነው - ልዑል ሎንኮኬላ ዲላሚኒ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ያመጣችው ለውጥ አስደናቂ ነው - ልዑል ሎንኮኬላ ዲላሚኒ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብና በሌሎች ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ያመጣችው ለውጥና ያስመዘገበችው ስኬት አስደናቂ መሆኑን የኢስዋቲኒ ኪንግደም የተፈጥሮ ኃብትና ኃይል ሚኒስትር ልዑል ሎንኮኬላ ዲላሚኒ ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን በኃይል ለማስተሳሰር ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠችበት ነው ብለዋል።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባኤው የኢስዋቲኒ ኪንግደም የተፈጥሮ ኃብትና ኃይል ሚኒስትር ልዑል ሎንኮኬላ ዲላሚኒ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአፍሪካ የውኃ መሰረተ ልማት ማስፋፋት ይበልጥ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።
ያለ ውኃ ልማት የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ማድረግ አይቻልም ያሉት ሚኒስትሩ የአፍሪካ ሀገራት በቂ በጀት በመመደብ በውኃ ላይ ያላቸውን ኢንቨስትመንት ከፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በራሷ አቅም ገንብታ ለውጤት ማብቃቷ እንዳስደነቃቸውም ገልጸዋል።
ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አፍሪካ አገራትም የሚተርፍ የፕሮጀክት አፈጻጸሙም በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ አፍሪካን በኃይል ለማስተሳሰር ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠችበት ስኬታማ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከኃይል መሰረተ ልማት ባሻገር በመንገድ እና ሌሎች የልማት መስኮች አርዓያ የሚሆን ለውጥ ማስመዝገቧን አንስተዋል።
ከስምንት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ መጥቼ ነበር፤ ኢትዮጵያ እንደዚህ አልነበረችም፤ አሁን ግን በሁሉም የልማት መስኮች ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥታለች ሲሉም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው በተመለከቱት ለውጥና የልማት ጉዞ መደነቃቸውንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ውጤት የአመራሩን የገዘፈ ሚና የሚመሰክር ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በአብነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።