ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ምህዳር በመፍጠር ለአፍሪካ የዲጂታል ስርዓት ሽግግር ሚናዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ምህዳር በመፍጠር ለአፍሪካ የዲጂታል ስርዓት ሽግግር ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም 2026 "የአፍሪካን የወደፊት ተስፋ በገንዘብ መደገፍ፣ የሥራ ዕድልና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ሽግግር" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተካሂዷል።



 

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚሁ ወቅት፤ አፍሪካ ሁሉን አቀፍ ሽግግር ለመጀመር ዝግጅት ላይ ሳትሆን ቀደም ብላ ወደ ሂደቱ መግባቷን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ሕዝብን ያቀፈ አንድ የገበያ ማዕከል የፈጠረ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት መስፋፋትና የስታርትአፕ ንቅናቄ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ያለውን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎችና ወኪሎች በዲጂታል ሥርዓት እየተሳተፉ መሆኑን በማንሳት፤ የአፍሪካን አካታች የዲጂታል ሽግግር የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ የአረንጓዴ ኃይል፣ የዲጂታል ሥርዓትና ክህሎትን በፋይናንስ መደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ሙሉ በሙሉ መተግበር የግድ ይላል ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ የውስጥ የገቢ አቅምን ማሳደግና ፈጠራን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በፖሊሲ ትንተና፣ በትብብርና በሌሎችም መስኮች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ዋና ጸሐፊው አረጋግጠዋል።


 

በአረብ ባንክ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ዋና ጸሐፊ ፋቲማ ፋሩክ (ዶ/ር)፥ አፍሪካ እምቅ ሀብት ያላት የወጣቶች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የአረብ ባንክ ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት በአረብ ካፒታል እና በአፍሪካ ቀዳሚ የልማት ትኩረቶች መካከል ድልድይ ሆኖ ሲያገልግል ቆይቷል ብለዋል፡፡

ባንኩ ከሰሀራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ አቅርቦት እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳማይላ ዙባይሩ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የሚከናወነው አካታች ሽግግር ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡


 

የሥራ ዕድል ፈጠራ የሽግግር ውጤት መሆኑን በማንሳት፤ ኢንዱስትሪ ደግሞ ልማትን በማፋጠን ከተማን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

በአምራችና አገልግሎት ዘርፎች የመንግሥትና የግል አጋርነትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ባንኮች ለልማት ፋይናንስ ድጋፍ ዝግጁ መሆን አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ባንኮች ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ዝግጁ ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ደረጃውን የጠበቀ የአደጋ ቅነሳ የፋይናንስ ምደባ ማድረግ ላይ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም