ቀጥታ፡

ለሕዝባችን የገባነውን ቃል፣ ሕዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ በብቃትና በውጤት ፈጽመናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሕዝባችን የገባነውን ቃል፣ ሕዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ በብቃትና በውጤት ፈጽመናል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው አገራዊና ከተማ አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶን እና የምርጫ ምልክት የሆነው "የስንዴ ነዶ" በአዲስ አበባ ደረጃ ይፋ ተደርጓል።


 

ምርጫ ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚገለጽበትና ሕዝብ በድምፁ መንግሥት የሚመሠርትበትም ሂደት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሕዝባችን የገባነውን ቃል፣ ሕዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ በብቃትና በውጤት ፈጽመናል ብለዋል።

በ7ኛው ዙርም ለሕዝባችን ቃል የምንገባው፣ ከተመረጥን ያለምነውን ሁለንተናዊ ብልፅግና ሌት ተቀን በመሥራት ያለምንም መሸራረፍ እንፈጽማለን ሲሉ ገልጸዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ማኒፌስቶ ትናንትን ማከሚያ፣ ዛሬን በአግባቡ መጠቀሚያ፣ ነገን መተለሚያና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት አገር ማሻገሪያ መመሪያችን ነው ብለዋል።


 

የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታችን የሆነው የስንዴ ነዶም የመደመር፣ የአንድነት፣ የተባብሮ መሥራት፣ የምርታማነት፣ የተምሳሌትነት፣ የልዕልና እና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ይህም በሁላችን፣ ከሁላችን፣ ለሁላችን ብልፅግናን የምናረጋግጥበት ምልክታችን ነው ያሉት ከንቲባዋ ስለሆነም ፣ ብልፅግና ቃሉን ይጠብቃል፤ ቃሉን ይፈጽማል፤ ሕዝቡን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ያደርጋል ብለዋል።

ዛሬ የብልፅግና ፓርቲያችንን የ7ኛው አገራዊና ከተማ አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶን እና የምርጫ ምልክታችን የሆነውን "የስንዴ ነዶ" በአዲስ አበባ ደረጃ ይፋ አድርገናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም