በዞኑ አርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና ጥራትን ለማስጠበቅ በተሰሩ ሥራዎች ለውጥ እየመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ አርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና ጥራትን ለማስጠበቅ በተሰሩ ሥራዎች ለውጥ እየመጣ ነው
ሐመር፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፡-በደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በዞኑ ሐመር ወረዳ ሻንቆ ቀለማ ቀበሌ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቱን ዛሬ መርቀው የከፈቱት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት ትምህርት ወሳኝ መሆኑን ነው ያነሱት።
መንግስትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል ።
ዛሬ የተመረቀው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በአርብቶ አደሩ አካባቢ የትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ ለተጀመረው ሥራ አንድ የለውጥ እርምጃ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል በአርብቶ አደሩ አካባቢ የትምህርት ተሳትፎ አነስተኛ እንደነበር አስታውሰው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በተደረገ የተቀናጀ ርብርብ ለውጥ ታይቷል ብለዋል።
ለዚህም አርብቶ አደሩ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ልጁን ማስተማር መጀመሩን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የሐመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ጋርሾ በበኩላቸው እንዳሉት ዛሬ የተመረቀው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት ያግዛል።
የወረዳው አስተዳደር ለትምህርት ቤቱ አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት ትምህርት ቤቱ የተጣለበትን ተልዕኮ እንዲወጣ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ለሕንፃ ግንባታው ድጋፍ ካደረጉት መካከል የሴንተር ኦፍ ኮንሰርን ድርጅት የሕፃናት ጥበቃና ትምህርት አስተባባሪ አቶ አማኑኤል ማቴዎስ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልፀዋል።
ግንባታው ሁለት መማሪያ ክፍሎች፣ አንድ ቢሮ እና ስቶር ከነ ሙሉ መማሪያ ቁሳቁስ ያካተተ መሆኑን አንስተው ለተማሪዎች ሙሉ የደምብ ልብስ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የዞኑና የወረዳ አስተዳደር የሥራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።