በክልሉ በተፈጥሮ አካላዊ የጤና ችግር ኖሮባቸው የሚወለዱ ህፃናት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተፈጥሮ አካላዊ የጤና ችግር ኖሮባቸው የሚወለዱ ህፃናት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው
ባህርዳር፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተፈጥሮ አካላዊ የጤና ችግር ኖሮባቸው የሚወለዱ ህፃናት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ‘‘በላቀ ተነሳሽነት ለኢትዮጵያ ልጆች’’ በሚል መሪ ቃል ችግሩን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአጋር አካላት ጋር የመከረበት መድረክ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ በወቅቱ እንደገለጹት በተፈጥሮ አካላዊ የጤና ችግር ኖሮባቸው የሚወለዱ ህፃናት ችግርን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል።
በሽታው ሲያጋጥም ታክሞ የሚድን መሆኑን ለህብረተሰቡ በማስተማር ከችግሩ ጋር ተያይዞ የሚወለዱ ህፃናትን በቀላሉ ወደ ህክምና በማምጣት እንዲድኑ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የቆልማማ ዕግር ችግር ከሚወለዱ አንድ ሺህ ህፃናት መካከል በአንዱ ላይ እንዲሁም የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ደግሞ ከ627 ህፃናት በአንዱ ላይ የሚከሰት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ከ2 ሺህ 300 በላይ የቆልማማ ዕግር ችግር ያላቸውን ህፃናት በማፈላለግ ተከታታይነት ያለው ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በየዓመቱ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን 300 ህፃናት በጤና ተቋማት ህክምና አግኝተው እንዲድኑ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም በደሴ ከተማ በሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲሁም በየካቲት 23 ቀን 2018 ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ጋምቢ ቲችንግ ሆስፒታል የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ህክምና በዘመቻ እንደሚሰጥ አመላክተዋል ።
በጤና ሚኒስቴር የስፔሻሊቲና ተሃድሶ አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ አቶ ኤርምያስ ሙላቱ በበኩላቸው በተፈጥሮ የጤና ችግር ያለባቸውን ህጻናት በሀገር ደረጃ ተገቢውን ህክምና አግኝተው እንዲድኑ እየተሰራ ነው።
ህክምና የሚሰጠውም ከጡንቻና ከአጥንት ጋር ተያይዞ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ላለባቸው፣ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ፣ የዕድገት ውሱንነት፣ የቆልማማ እግር ችግርና ሌሎች በሽታዎች መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልም ከእርግዝና በፊትና በዕርግዝና ወቅት እናቶች የህክምና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው ጠቁመው ከወለዱ በኋላም ችግሩ ሲታወቅ ፈጥኖ በማሳከም ማዳን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጤና ሚኒስቴርም ክልሉ ችግሩን ለመከላከል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ዕገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በመድረኩም ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልሉ ጤና ቢሮ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።