ቀጥታ፡

በነቀምቴ ከተማና አካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን አገልግሎትን ለማሳለጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ነቀምት፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ)፡- በነቀምቴ ከተማና አካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን አገልግሎትን ለማሳለጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት  ሥራ አስኪያጅ  አቶ ገላና መኮንን፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በከተማዋ በተለይም በመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የከተማዋን ህዝብ ብዛት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በነቀምቴ የዲጋ፣ ጫንጮ እና ሀዲያ የውሃ ግድቦችን አቅም በመደመር ለነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የሳኒቴሽን አገልግሎትን ለማሳለጥም በክልሉ መንግስት በጀት የሳኒቴሽን ፕሮጀክት ግንባታ እየተካሄደ ስለመሆኑ አንስተው ይህም የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን በማሳለጥ ለከተማዋ ውበትና ፅዳት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በነቀምቴ ከተማ የውሃ እና ፍሳሽ ፅህፈት ቤት የውሃ ምርት እና ጥራት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉነሽ በቀለ፤ ለከተማዋ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት ላይ በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የውሃ አቅርቦትን ከማሳደግም ባለፈ በውሃ ውስጥ የሚገኙ ማዕድናት መብዛት እና ማነስ የሚያደርሰውን የጤና ችግር መፍታት በሚያስችል መልኩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ከውሃ አቅርቦትና ተደራሽነት ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የውሃ ጥራትና አቅርቦት ከፍተኛ መሻሻል በማሳየቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ አያልነሽ ታደሰ፤ ከዚህ በፊት በቂ የሆነ የውሃ አቅርቦትና ስርጭት ስላልነበር ለችግር፣ እንግልትና ወጪ ይዳረጉ እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ላይ ግን እነዚህ ችግሮች እየተቃለሉ ከፍተኛ መሻሻል ስለመኖሩ ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች አቶ አበራ ነጋሳ እና  አቶ ደሞዜ ተስፋ፤ የውሃ አቅርቦትና ስርጭት ችግሩን ለመፍታት የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ የውሃ አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ የሚታይ ለውጥ መምጣቱን ገልጸው ቀጣይነት እንዲኖረውም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም