ቀጥታ፡

በክልሉ የመማር ማስተማር ሥራን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት ተደርጓል

ሆሳዕና፤የካቲት 9/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመማር ማስተማር ሥራን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በሁለተኛው ግማሽ ዓመት የዘርፉ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል፡፡ 


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንዳሉት፤ በክልሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ሥራን ለማስፋት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።

በዚህም ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያየ ደረጃ ባሉ ትምህርት ቤቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ ትምህርቶችን በመስጠት ተማሪዎች አስፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ጊዜው የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመሆኑ የመማር ማስተማር ሥራውን በቴክኖሎጂ መደገፍ ፍትሀዊ ተወዳዳሪነትን ለማስፈን ያለው ጠቄሜታ የጎላ በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን ነው አቶ አንተነህ ያመለከቱት፡፡

ለዚህም ስኬት በትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ቤተ ሙከራዎችን ጨምሮ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ግብዓቶችን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አንተነህ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ በክልሉ በተማሪዎች ውጤት ላይ የታየውን መሻሻል ለማስቀጠል የሚያስችል መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመው  ለዚህም በተለይ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ላይ ጠንካራ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የስልጤ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹኩራላ አወል በበኩላቸው፤ በዞኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በሚሰሩ ሥራዎች ላይ የተስተዋሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በጥናት የተደገፈ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ከተማሪ ወላጆች፣ መምህራን እና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ውጤትን መሰረት ያደረገ ክትትልና ድጋፍ ላይ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይም የመማር ማስተማር ስራውን በቴክኖሎጂ ለማገዝ አስፈላጊ ግብአቶች ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ነው ያብራሩት።

በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተጀመረው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ደግሞ ሌላው የጉባኤው ተሳታፊ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም ናቸው፡፡


 

በዚህም በዘንድሮው ዓመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን በተለይም የመማር ማስተማር ስራውን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ግብአቶች የማሟላት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ሥራ ማስፋፋትም ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ የቢሮው፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም