ቀጥታ፡

በክልሉ አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብና ተኪ ምርቶችን በማምረት ውጤት ተመዝግቧል

ባህር ዳር፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብና ተኪ ምርቶችን በማምረት ውጤት  መመዝገቡን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ  አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት  በክልሉ ዘርፉን ለማሳደግ የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት እና የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ታቅዶ እየተተገበረ ነው። 

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት  አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብና ተኪ ምርቶችን በማምረት ውጤት  መመዝገቡን ተናግረዋል።


 

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 183 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ከ1 ሺህ 800 በላይ አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ መሳብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ለባለሃብቶቹ ቦታ ከማመቻቸት ባለፈ ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ ተኪ ምርቶችን በማምረት ሰፊ ስራ መሰራቱን አንስተው በግማሽ ዓመቱ ከ321 ሺህ ቶን በላይ የኢንዱስትሪ ተኪ ምርቶችን በማምረት ከ366 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል። 

እንዲሁም 43 ሺህ ቶን የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ112 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምም ከ59 በመቶ ወደ 62 በመቶ በላይ ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በዘርፉ ከ47 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በዘርፉ የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል መቻሉን ጠቁመው በተለይም በርካታ አገልግሎቶችን በባህር ዳርና ደሴ ከተሞች ወደ ሞሶብ አንድ ማዕከል በማስገባት ባለሃብቶች ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰዋል። 

በቀጣይ በዘርፉ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ከማሳደግ ባለፈ የተገኙ ስኬቶችን የማጠናከርና የተስተዋሉ ድክመቶችን የማስተካከል ስራ በትኩረት እንደሚከናወን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም