የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ስኬት በፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃብት ለማፍራት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ስኬት በፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃብት ለማፍራት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ስኬት በፈጠራና የቴክኖሎጂ ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃብት ለማፍራት ዕድል መፍጠሩን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ገለጸ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ 80ኛውን ዓለም ዓቀፍ የኮምፒውተር ቀንን አስመልክቶ የመጀመሪያው የስማርት ሲስተም ሶሊዩሽን ጉባኤ አካሂዷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዲጂታላይዜሽን መሠረተ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ወንደሰን ሙሉጌታ፤ ኮሌጁ ካለፉት አርባ ዓመታት ጀምሮ በኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ብቁ ሙያተኞችን እያፈራ ይገኛል ብለዋል።
የዓለም ዓቀፍ የኮምፒውተር ቀን ዝግጅቱም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የደረሰችበትን ዕድገት በመቃኘት የተወዳዳሪነት አቅምን ለማሳየት እንደሚረዳ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት አስተዳደር የማሻሻያ እርምጃዎች የኮሌጁን የቴክኖሎጂ አቅም በማጎልበት ለኮምፒውተር ሳይንስ የጥናትና ምርምር ሥራ ዕድገት ምቹ ዕድሎችን እንደፈጠረ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የተወዳዳሪነት አቅም ግስጋሴ በዕውቀትና ክህሎት የበቃ የሰው ሃይል ለማፍራት ምቹ መደላድል እየተፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አምሳለ ዘላለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን ሥርዓት አቅም የሚሆን የሰው ሃብት እያፈሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም በዘርፉ የላቀ ልምድና ተሞክሮ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ የዲጂታልና ኢኖቬሽን ልማት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዳግማዊ ለማ፤ ''የኮምፒዩተር ዕድገት በኢትዮጵያ ከየት ወደ የት'' በሚል የመነሻ ጽሑፋቸው የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት ዕድገት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ፈጣን ዕድገት በሚያስመዘግበው የዲጂታል ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ በቴክኖሎጂ መስክ የላቀ ዕውቀትና ክህሎት የተላበሰ የሰው ሃይል የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።