ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ፕሮጀክቶች የጽዱ ኢትዮጵያን ኢንሼቲቭን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግሩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ፕሮጀክቶች የጽዱ ኢትዮጵያን ኢንሼቲቭን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግሩ ናቸው
ድሬደዋ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ በአምስት የኢትዮጵያ ከተሞች የሚከናወኑት ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ፕሮጀክቶች የጽዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሻግሩ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበለት የድሬደዋ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ እና ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሯል።
ግንባታውን ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፣ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና ሌሎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።
ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ከተሞች ውብ፣ ፅዱና ማራኪ የመኖሪያ እና የስራ ከተሞች ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው።
ፅዱ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግና በአፍሪካ ተመራጭ ከተሞችን ለመፍጠር በመተግበር ላይ የሚገኙ የልማት ኢንሼቲቮች በተሳካ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ማሳያ በኮሪደር ልማት እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶች ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ውጤታማ የጽዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቮች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ አምስት ዋና ዋና ከተሞች ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና ማጣሪያ የመገንባት ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
በድሬደዋ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን በማስረዳት።
የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ወደ ግንባታ ለሚገባው የዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት አስተዳደሩ 13 ሄክታር መሬት አዘጋጅቶ ማቅረቡን ጠቁመዋል።
ለልማቱ ለተነሱት አርሶ-አደሮች ምትክ ቦታና ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መሰጠቱን ገልፀው፣ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ፣ በጀትና ጥራት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
በድሬደዋ እየጨመረ የሚገኘውን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የመጠጥ ውሃና ንጽህና አገልግሎትን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መሐመድ ሙሴ ናቸው።
የድሬደዋ ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ እና ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታን በ18 ወራት በማጠናቀቅ የከተማዋን የፍሳሽ አወጋገድ ሥርአት በማዘመን ውብና ፅዱ ከተማ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።