ቀጥታ፡

ችግሮችን በምክክርና በውይይት በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ መደላድሎችን ለማስፋት እንሰራለን- የሀይማኖት አባቶች

ሆሳዕና ፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ) ፡-ችግሮችን በምክክርና በውይይት በዘላቂነት ለመፍታትና የማህበረሰብን ትስስር ለማጎልበት የሚያስችሉ መደላድሎችን ለማስፋት እንደሚሰሩ የሀይማኖት አባቶች ገለፁ፡፡

በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን  የሚጠበቀው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሊካሄድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተደርሷል።

በእስካሁኑ ሂደትም ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ የውይይት አጀንዳዎችን አሰባስቦ የማደራጀት ሥራ  እየተከናወነ ሲሆን ለስኬታማነቱ የሁሉንም አካላት ትብብርና ሀላፊነት ይጠይቃል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ይህንኑ በተመለከተ በሆሳዕና ከተማ በተካሄደው 6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የተሳተፉ  የሀይማኖት አባቶች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የሀይማኖት አባቶቹም  ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ የምክክር ባህሎች እንዲዳብሩ እንሰራለን ብለዋል ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ሰብሳቢና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከፄዴቅ እንዳሉት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ምክክርና ውይይቶች እንዲካሔዱ በትኩረት እንሰራለን ።

ሀገራዊ ምክክር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምቹ ምህዳር የሚፈጥር መሆኑን አንስተው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ  ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሆሳዕና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ስዩም ፍራንሷ በበኩላቸው፤ በዜጎች መካከል አልፎ አልፎ የሚከሰት አለመግባባትና ግጭት ተፈጥሯዊ መሆኑን አንስተው የመፍቻ መንገዱ ጥፋት ሊሆን አይገባም ብለዋል ፡፡

መደማመጥና መመካከር መተማመንን የሚያጎለብት ከመሆኑ ባሻገር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም የሀይማኖች አባቶች  ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ የሚጠበቅብን በመሆኑ በልዩ ትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

አለመግባባቶችን በመሳሪያ አፈሙዝ ለመፍታት መሞከር ማንንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ባለመሆኑ ትውልዱ ከዚህ በመራቅ ችግሮችን በምክክር  የሚፈታበት አካሄድ ላይ እንዲያተኩር ማስተማርና ማስገንዘብ ይገባናል ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ የሰላምና ልማት ስራዎችን ለማሳካት  የምክክር ሂደቱን ማጠናከር ይገባል ያሉት ደግሞ የሆሳዕና ዙሪያ የወንጌላውያን አማኞች ካውንስል አስተባባሪ ኮማንደር አዲሴ ፈይሳ ናቸው

ለዚህም ስኬት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያሳተፈ የምክክር ሂደት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው  ለስኬታማነቱ በተሻለ መንገድ እንሰራለን ብለዋል፡፡

የምክክር ሂደቱ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥን ያለመ በመሆኑ ሂደቱ በታለመለት መንገድ ተፈፃሚ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚና የሀጂና ኡምራ ዘርፍ ኃላፊ ኡስታዝ ፃዲቅ ወጌቦ በበኩላቸው የመለያየት እሳቤን ከመዝራትና ግጭቶችን ከማባባስ ይልቅ በሰላማዊ መንገድ ተቀራርቦ መስራት የሚቻልበት ምቹ ምህዳር በምክክር ኮሚሽን አማካኝነት የተጀመሩ ስራዎች ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡

የማህበረሰቡን ትስስር በማጠናከር ፣ ዘላቂ ሰላምን በማፅናትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከማድረግ አኳያ የሀይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለምክክሩ ስኬታማነት የሚጠበቅብንን ሚና እንወጣለን ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲያጋጥሙ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

ምክክሩ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ እድሉን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም