ኢትዮጵያ በየቀኑ የመሪነት ብቃቷን የምታሳይ ሀገር ሆናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በየቀኑ የመሪነት ብቃቷን የምታሳይ ሀገር ሆናለች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በሁሉም መስክ በየቀኑ የመሪነት ብቃቷን የምታሳይ ሀገር ሆናለች ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የተመድ የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የተቋቋመውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ማዕከል (AI UniPod) በይፋ አስጀምረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የተመድ የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ፥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ ፈጠራ ማዕከል “AI UniPod” በይፋ ሥራ መጀመሩ የአፍሪካን እያደገ የመጣ በራስ መተማመን የሚያሳይና ህልማችንን እውን ያደረገ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ያላመረትነውን እንድንጠቀም ያመረትነውን ደግሞ ለሌላው እንድንሰጥ ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል።
አሁን ለውጥ እየመጣ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፥ ቴክኖሎጂን የምናይበት መንገድ እየተቀየረ ነው፤ ለዚህም አፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን ፈጣሪ፣ ቀራጭና መሪ እንድትሆን እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም ለሁሉን አቀፍና ቀጣይነት ላለው ልማት የሚበጅ ቁልፍ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በተጠናቀቀ ማግስት ይህ ማዕከል መከፈቱ የአፍሪካ መሪዎች በአጀንዳ 2063 ያስቀመጡትን የፈጠራ፣ የቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ልማት ግብ እንደሚያንጸባርቅ አንስተዋል።
እንደ “AI UniPod” ያሉ ተነሳሽነቶች ተግባራዊ የፈጠራ ስራዎች እንዴት ለልማት መፍትሄ እንደሚሆኑ የሚያሳዩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ተሳትፎ እውን መሆኑን በመጥቀስ፥ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በየቀኑ የመሪነት ብቃቷን የምታሳይ ሀገር መሆኗን በማንሳት፥ እንዲህ አይነት ስትራቴጂካዊ ስራዎችን እንድናሳካም የሀገሪቱ መንግሥትና ተቋማት ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል።
የማዕከሉ ዓላማ ሰው ሰራሽ አስተውሎት አፍሪካን ይለውጣል ወይ የሚለው ሳይሆን አፍሪካን እንዴት መለወጥና ምን ፋይዳ ማምጣት አለበት የሚለው ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በመላው አፍሪካ በአካዳሚው፣ በመንግስትና በገበያው መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የፈጠራ ማዕከላት ላይ ኢንቨስት እያደረገ ነው ብለዋል።
ከእንግዲህ የምርምር ስራዎች መደርደሪያ ላይ ተቀምጠው አይቀሩም ያሉት ሀላፊዋ፥ ይልቁንም በተግባር ተተርጉመው ህዝባችን የሚጠቅሙበት ወሳኝ ጉዞ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ዛሬ የተመረቀው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ ፈጠራ ማዕከል መሰረቱን ኢትዮጵያ አድርጎ አህጉራዊ ሚና እንዲኖረው መታቀዱን ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን፣ የምግብ ዋስትናን፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በሚመለከት አፍሪካ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም እንደዚህ ያሉ ማዕከላት ወሳኝ መሆናቸውንም አፅንኦት ሰጥተዋል።