ቀጥታ፡

በሁሉም መስክ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራው ሥራ ውጤት ተመዝግቧል

ዲላ፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ):-በሁሉም መስክ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራው ሥራ ውጤት መመዝገቡን የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አስታወቀ። 

"በሴቶች ተሳትፎ የፀናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል የሴቶች ክንፍ የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ሥራ አስፈጻሚ መላኬ አለማየሁ በወቅቱ እንዳሉት፤መንግስት ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራቱ ስኬት ለማስመዝገብ ተችሏል።

በተለይ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር ሴቶች ከጠባቂነት ተላቀው የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።

ሴቶች የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ከመሆናቸው ባለፈ ለሰላም እሴት ግንባታ ድርሻቸው የጎላ መሆኑ አንስተው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆን የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

"ሴቶች በምርጫው በነቂስ በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ ልምምድን ልናጠናክር ይገባናል " ነው ያሉት።

በዞኑ ሴቶች በከተማ ግብርና፣ በሌማት ቱሩፋትና መሰል የልማት ሥራዎች ያላቸው ተሳትፎ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ያሸጋገራቸው መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሀገር አንድ መገለጫ መሆኑን አንስተው ሴቶች በዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የፀናችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረግ ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ አመልክተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የዲላ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊና የሴቶች ክንፍ ከፍተኛ አመራር የካቲት ጥላሁን በበኩላቸው፤ ሴቶች ጠንካራ የመሪነት አቅማቸውንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።


 

በቀጣይም ይህን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለ7 ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰኬታማነት ሴቶች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።  

በመድረኩ ከፓናል ውይይት በተጨማሪ የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን በየደረጃው ያሉ የሴቶች ክንፍ አባላትና አመራሮች እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪና ታዋቂ ሴቶችም ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም