ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ጠንካራ መሰረት ይዞ እንዲቀጥል የበኩላችንን እንወጣለን- የምክር ቤት አባላት

አርባምንጭ፤የካቲት 9/2018 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ጠንካራ መሰረት ይዞ እንዲቀጥል የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መርሃ ግብር መሰረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

በዚህም መሰረት በቅድመ ምርጫው የፓርቲዎች የእጩዎች ምዝገባ በመካሄድ ላይ ሲሆን በቀጣይነት የመራጮች ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ይታወቃል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ጠንካራ መሰረት ይዞ እንዲቀጥል፤ በምርጫው ሂደት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ ዓለምገነት ላቀው፤ ጠቅላላ ምርጫውን ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እኩል ውድድር የሚካሄድበትን አውድ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ዝግጅት አድንቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫው ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ለማድረግ ከወዲሁ እያደረጉት ያለው ዝግጅት መልካም ጅምር መሆኑን አንስተዋል።

ሌሎች የምክር ቤት አባላት አቶ ደስታ አዶ እና አቶ ማሙሽ ሲማያ፤ ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ከምርጫ ቦርድ በተጨማሪ ፓርቲዎች ለሰላምና ፍትሃዊ ውድድር ያላቸው ቁርጠኝነት እንዲሆም የህዝቡን ጠንካራ ተሳትፎ የግድ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለምርጫው ስኬትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት የሁሉም አካላት ጥረትና ትብብር እንዳለ ሆኖ እንደ ምክር ቤት አባልነታቸው የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም