ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢነርጂ አማራጮች አገልግሎት እንዲሰጡ መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው

ጋሻሞ/ሚርቃን፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢነርጂ አማራጮች ለምተው አገልግሎት እንዲሰጡ መንግስት ትኩረት መስጠቱን  የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሶማሌ ክልል ጋሻሞ እና ምርቃን ከተሞች የሶላር ሃይል ፕሮጀክቶች ተጠናቀው የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

በምረቃ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)  እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የታሰበውን ብልጽግና ያለበቂና አስተማማኝ ኢነርጂ ማሳካት ስለማይቻል የኢትዮጵያ መንግስት ለኢነርጂ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል።


 

በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢነርጂ አማራጮች እንደሚገኙ ገልጸው ይህንን በአግባቡ በማልማት ለአገልግሎት ለማዋል መንግስት የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው ለሚገኙ ከተሞች የሶላር ሃይል ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ጋሻሞ ከተማ የተመረቀው የሶላር ሃይል አገልግሎት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ  ወጪ የተደረገበት ሲሆን ለስድስት ሺህ አባወራዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በሚርቃን ከተማም አገልግሎት መስጠት ለጀመረው የሶላር ሃይል 170 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።

ይህም  ለ1ሺህ 200 አባወራዎች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሶማሌ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ  ሹክሪ በበኩላቸው፤ የተመረቁት የሶላር ሃይል ፕሮጀክቶች የከተሞቹን  እድገት የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ተናግረው በቀጣይም በሌሎች የክልሉ ከተሞች ተደራሽ ይሆናሉ ብለዋል።

የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ እድመን መሀመድ፤ የኢነርጂ አገልግሎቱ ህብረተሰቡ ጥራትና ዘላቂነት ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ አገልግሎትም የከተሞቹ እድገትና ንግድ እንዲፋጠን የበለጠ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም