ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምርና ቴክኖሎጂ ፈጠራ መሪ እንድትሆን ይሠራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምርና ቴክኖሎጂ ፈጠራ መሪ እንድትሆን የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የተቋቋመውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ማዕከል (AI UniPod) በይፋ አስጀምረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር)፥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ ፈጠራ ማዕከሉ ሥራ መጀመር በኢትዮጵያ ዲጂታል ምርምር ጉዞ ውስጥ ትልቁ ብሔራዊ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

በተቀናጀ አጋርነት እውን የሆነው ይህ ማዕከል ሀገራችን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምርና ልማት ያላትን አቅም እንደሚያጠናክርም ጠቁመዋል።

ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሀገሪቱ ቀዳሚ የምርምር ተቋምነቱና ካለበት ኃላፊነት ጋር ቀጥታ የሚጣጣም ነው ብለዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው ይህ የፈጠራ ማዕከል በዕውቀት ላይ የተመሰረተና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን የአካዳሚክ መሰረትን፣ የምርምር እውቀትንና የሰው ኃይልን እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ ምህንድስናን፣ ግብርናን፣ ጤና ሳይንስንና የመንግስት ፖሊሲን የሚያስተሳስር ዘርፈ-ብዙ መስክ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእነዚህ ዘርፎች የድህረ-ምረቃ ስልጠናዎችን እያስፋፋ እንደሚገኝ ጠቁመው በሰው ሰራሽ አስተውሎት የመጀመሪያውን የዶክትሬት ዲግሪ መርሃ-ግብር በመጀመር ምሁራንን እያፈራ ነው ብለዋል።

የዚህ ማዕከል መመሥረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አጀንዳዎች፣ በተለይም ከዲጂታል ኢትዮጵያና ከብሔራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፖሊሲ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንስተዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በግብርና ዘርፍ መረጃን መሰረት ያደረገ የሰብል ክትትልና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም አቅምን ማሳደግ፣ በጤና ዘርፍ የበሽታ ምርመራና የሕክምና ጥራትን ማሻሻል፣ በትምህርት መስክ ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ትንታኔዎችን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

ዛሬ ሥራ የጀመረው የፈጠራ ማዕከልም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ስርዓት አካል ሆኖ እንደሚያገለግል አንስተዋል።

የማዕከሉን እንቅስቃሴዎች ከድህረ-ምረቃ ምርምሮች ጋር በማስተሳሰር፣ የአእምሯዊ ንብረት መብቶችን ባከበረ መልኩ የፈጠራ ውጤቶች ወደ ገበያ የሚወጡበትን መንገድ እናመቻቻለን ነው ያሉት።

አፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያላት ተሳትፎ ከተጠቃሚነት ወደ አምራችና አበርካችነት ሊሸጋገር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአፍሪካን መረጃዎችና ቋንቋዎች ያላካተቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶች ፋይዳቸው አነስተኛ በመሆኑ የራስን የምርምር አቅም መገንባት ስትራቴጂካዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፈጠራና የምርምር ስነ-ምግባርን የተከተሉና አህጉራዊ እውነታን ያገናዘቡ የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ረገድ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም