ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት እንደሚረዱም አምባሳደር ዳረን ዌልች አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ (ፒኦኤ) ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።
በቅርቡ የዩናይትድ ኪንግደም የኮመንዌልዝ፣ የልማት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር የመጀመሪያውን የአፍሪካ ጉብኝት በኢትዮጵያ መጀመራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይህም የሀገራቱ ወቅታዊ ግንኙነት እያደገ ለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚሁ ወቅትም የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስምምነቶች መፈረማቸውን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም መኖሩን ጠቁመው፤ ይህንን ዕድል ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የምታደርገውን ያላሰለሰ ጥረትና የምትከፍለውን መስዋዕትነትም አድንቀዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገሯ ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እየከፈለች ለሚገኘው መስዋዕትነት ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ እያከናወነች ያለው ተግባር የሀገሪቷን ታላቅነትና ለጎረቤቶቿ የምትሰጠውን ታላቅ ስፍራ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሰፊ የልማት አቅም ያለው የአፍሪካ ቀንድ ወደ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና እንዳላትም ጠቅሰዋል።
ቀጣናው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ሰፊ ጥቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ወሳኝ ሚና እንደምትጫወት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች ያለች እና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት በጎ አስተዋጽኦ የምታበረክት ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚረዱ ገልጸው፤ የባህር በር ለማግኘት የያዛቸውን ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች አጠናክራ እንድትቀጥል ጠቁመዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ኢንቨትመንት እና ንግድ ግንኙነት ለማሳደግ እየሰራች ስለመሆኑም አብራርተዋል ::