ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የልማት ስኬት ለአፍሪካ ሀገራት የዕድገት ጉዞ በአርዓያነት የሚወሰድ ውጤት ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የልማት ስኬት ለአፍሪካ ሀገራት የዕድገት ጉዞ በአርዓያነት የሚወሰድ ውጤት መሆኑን የሩዋንዳና የኢስዋቲኒ ዲፕሎማቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ የልማት ግብን በማፋጠን ለቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገትና ትስስር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደላው ገልጸዋል።

የፓን አፍሪካኒዝም መሠረቷ የኢትዮጵያ የልማት ውጤቶችም ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በአርዓያነት የሚወሰዱና ሀገሪቱን አፍሪካዊት ዱባይ የሚያሰኟት መሆናቸውንም አንስተዋል።

39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ”ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በሕብረቱ ጉባኤ የተገኙት የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኦሊቪየር ዣን ፓትሪክ እና በኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢስዋቲኒ አምባሳደር ማላባ አሊ ማምባ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኦሊቪየር ዣን ፓትሪክ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ምስረታና ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ጉልህ አበርክቶ ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጀምሮ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ በማስቻል ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን አንድነትና ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልነት ታሪካዊ ልምድና ስኬቷን እንደምታስቀጥል እምነቴ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር ምሳሌ የሚሆን አስደናቂ የልማት ስኬት እያዝመዘገበች እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢስዋቲኒ አምባሳደር ማላባ አሊ ማምባ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አስደናቂ የመሰረተ ልማት ስኬቶችን እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ስኬቶች አዲስ አበባን የአፍሪካ ዱባይ እያደረጋት እንደሚገኝም ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

በቀጣይም ኢስዋቲኒ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር በማጠናከር የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለውሃ ሃብትና ንጽህና አጠባበቅ የሰጠው ትኩረትም የአህጉሪቱን ዜጎች የውሃ መሰረተ ልማት ለማፋጣን ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

በራስ አቅም የተገነባው የሕዳሴ ግድብም አህጉራዊ የልማት ግብን በማፋጠን ለቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም