ኢንስቲትዩቱ አርብቶ አደሮችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ስራዎችን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ አርብቶ አደሮችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ስራዎችን እያከናወነ ነው
ጎዴ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ አርብቶ አደሩ ማሕበረሰብ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገርና የስራ ባህል ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለፀ።
የኢንስቲትዩቱ የስራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ምርትና ምርታማነትን እያጎለበቱ የሚገኙ አርብቶ አደሮችን የስራ ተግባራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ሲኒየር ዳይሬክተር ዳኛቸው ሉሌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የግብርና ዘርፉን የሚያሻግሩ ፕሮጀክቶችን በማበልጸግ ተግባራዊ እያደረገ ነው።
በተለይም በጥናት ላይ ተመስርቶ የሚያከናውናቸው ተግባራት የዘርፉን ማነቆዎችን ለመፍታት ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኢንስቲትዩቱ የሚበለጽጉት ፕሮጀክቶች የግብርና ምርትን በማሻሻልና ገበያ ተኮር የልማት እድሎችን በመፍጠር ሰፊ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን አክለዋል።
በተለይም የአርብቶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት በማጎልበት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም በጎብኝቱ ወቅት መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታና ግብይት፣ በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ በአግሪ ቢዝነስ ልማት እና በዲጂታል ግብርና ላይ 300ሺህ ግለሰቦችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል።
በተለይ በማህበረሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ የተከናወኑ ተግባራት ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በዞኑ የሰው ሃብት፣ መሬት፣ ውሃና ሌሎች ጸጋዎችን በማቀናጀት ህዝቡን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ያሉት ደግሞ በሶማሌ ክልል የሸበሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዲ ፋራህ ናቸው።
በዚህም በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬና ሌሎችን በስፋት በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርቱ ለገበያ እንዲቀርብ በማድረግ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ለማህበረሰቡ ድጋፍ በማድረግ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን አንስተው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በፕሮግራሙ ታግዘው በልማቱ ከተሰማሩት መካከል በሸበሌ ዞን በርአኖ ወረዳ በርቱቆራህ ቀበሌ ከፊል አርሶ አደር ገራድ አብዲ ፤በማህበር ተደራጅው ባገኙት መሬትና ዘር በመታገዝ የእንስሳት መኖ እያመረቱ መሆኑን ይገልፃሉ።
የመኖ ምርቱን ለእንስሳቱ በምግብነት በማዋል እና ዘሩንም ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ተረጂነትን የማስቀረት ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ከፊል አርሶ አደር ዘሃራ መሀመድም በመደራጀት በቆሎና ሽንኩርት የማምረት ስራን መጀመራቸውን አመልክተው ምርቱም እየደረሰ እና ተስፋ እየሰጠን ነው ሲሉ ገልጸዋል።የግብዓትና ሙያዊ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።