ኢትዮጵያ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መሻት ወደ ወሳኝ የተግባር ምዕራፍ ተሸጋግራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መሻት ወደ ወሳኝ የተግባር ምዕራፍ ተሸጋግራለች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሩቅ ከመሻት ወደ ወሳኝ የተግባርና የስኬት ምዕራፍ መሸጋገሯን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ማዕከልን በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ባላቸው ራዕይና በሰጡት ወሳኝ አመራር በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞም ከሀገሪቱ ወሳኝ የእድገት ምሰሶዎች አንዱ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ ማመጣቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምርን፣ ልማትንና አጠቃቀምን እንዲመራ የተቋቋመ፣ በዚህም ለውጥ ያመጣ ተቋም ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አቅም በመገንባት፣ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን በማፍለቅ ለፈጠራ ሥራ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር ሰጪነት በአፍሪካ ቀዳሚና ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተቋማት አንዱ ለመሆን መብቃቱንም ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የፓተንት መብት ያገኙ የጡት ካንሰር መመርመሪያ ቴክኖሎጂና የቡና ዘር መለያ ሥርዓት ኢንስቲትዩቱ ካፈለቃቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶች መካከል እንደሆኑ አስረድተዋል።
ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ ፈጠራ ማዕከል “AI UniPod”፥ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማዕከል ለማድረግ የታለመው ጉዞ አካል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስታርታፖች ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የሚሆኑ መፍትሄዎችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲያመርቱ አቅም እንደሚፈጥርም ጠቅሰዋል።
የመረጃ ሉዓላዊነት ከሀገር ሉዓላዊነት ጋር የማይነጣጠል መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን መረጃ እንደ ውድ ማዕድናት የሀገር ሀብት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለዲጂታል መሰረታዊ ፍላጎቶቿ በሌሎች ላይ ጥገኛ የሆነች ሀገር፣ ስለ ሙሉ ሉዓላዊነት መናገር እንድማትችል በማንሳትም የዲጂታልና የመረጃ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ሥራችን ነው ብለዋል።
ማዕከሉ የማወቅ ጉጉት ላላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በፍጥነት ማደግ ለሚፈልጉ ስታርታፖችና የዕውቀትን ድንበር ለሚያሰፉ ተመራማሪዎች የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወጣቶች ከስራ ፈላጊነት ወደ ስራ ፈጣሪነት፣ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ቴክኖሎጂ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ማድረግ ግባችን ብለዋል።
የሰው ሰራሽ የዩኒቨርሲቲ ፈጠራና ምርምር ማዕከል እውን መሆን ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሻቷን ወደ ተጨባጭ ምዕራፍ ያሸጋገረችበት መሆኑንም አክለዋል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዩኒቨርሲቲ ፈጠራ ማዕከሉ እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የፖሊሲ አመራርና ቴክኒካዊ አቅጣጫ በመስጠት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ልህቀትና የምርምር አቅም በማቅረብ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ዓለም አቀፍ ትስስርንና የልማት ልምድን በማካፈል በትብብር ሠርተዋል።