ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በተያዘው አመት ከ120 በላይ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ለምተዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በዚህ አመት የአካባቢውን እምቅ ሀብትና አቅም በመጠቀም ተጨማሪ 120 አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ለምተው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

በብዝሃ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ በመንግስት ትኩረት ካገኙ ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው።


 

በብዙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች በሚታወቀው በኦሮሚያ ክልልም ዘርፉን በማልማት፣ በማስተዋወቅና የጎብኚዎችን ቆይታ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴት ልማት ዳይሬክተር ኦላና ተሾመ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ ክልል በዚህ አመት የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጨመርና የቱሪስት ቆይታን ለማራዘም የሚያስችል የተለያዩ ተግባራት በኢንሼቲቭ ተከናውነዋል።


 

የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት የቱሪስት ፍሰትና ቆይታን ለማራዘም መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት ጎን ለጎን በተለይ በየአካባቢው ያለውን የባህላዊ ምግቦች፣ አልባሳት፣ ጭፈራዎች፣ ታሪክና የኪነጥበብ ስራዎችን የማልማት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ በየጊዜው የቱሪስት ፍሰትና የቆይታ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል በዚህ አመት የአካባቢውን ማህበረሰብ በማነቃቃትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአንድ ወረዳ አንድ መስህብ እንዲኖር ለማድረግ በንቅናቄ በተሰራ ስራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ነው አቶ ኦላና የተናገሩት።

በዚህም እስካሁን በአካባቢው ያለውን እምቅ ሀብትና አቅም በመጠቀም ከ120 በላይ ተጨማሪ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ለምተው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ገልጸዋል።

ልማቱ በወረዳ፣ በዞንና ከተማ አስተዳደር አቅም መሰራት መቻሉንም አክለዋል።


 

በቡኖ በደሌ የደንጋዋጅ፣ በቦረና ዞን የቦቄሶዳ፣ በምስራቅ ሸዋ የበሰቃና ቆቃ ሀይቆች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን የፖርቹጋል ድልድይ፣ በቄለም ወለጋ ሜጢ፣ በምስራቅ ወለጋ በሶርጋና በጅማ ደግሞ የቦዬ ሀይቆችን እንደማሳያነት አንስተዋል።

በየመስህቦቹ አካባቢዎች የቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ ከ24 ሺህ በላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ሆቴሎችና ሎጆችን በማስፋፋት ጥራት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛሉ ብለዋል።

እንዲሁም በክልሉ ያሉት ሆቴሎች ደረጃቸው እንዲሻሻል በማድረግ የቱሪስት ፍሰትን በመጨመርና ቆይታቸውን በማራዘም በቱሪዝም ዘርፉ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም