በጥናት ላይ የተመሠረቱ የግብርና ማሻሻያ ሥራዎች በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ የምርት ዕድገት እያስመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጥናት ላይ የተመሠረቱ የግብርና ማሻሻያ ሥራዎች በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ የምርት ዕድገት እያስመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦በጥናት ላይ የተመሠረቱ የግብርና ማሻሻያ ሥራዎች በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ የምርት ዕድገት እያስመዘገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የግብርናውን ዘርፍ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ በዘንድሮው የበጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ 7 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የተያዘውን ዕቅድ 78 በመቶ በማሳካት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 999 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
ለግብርና ምርታማነት ዕድገቱም ጥናትና ምርምር፣ ለአርሶ አደሮች የሚደረግ የግብዓትና የዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ግብዓት አቅርቦት የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለግብርና ዕድገት መሰረት የጣሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማካሄድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው።
የኢትዮጵያን የግብርና ሥርዓት ለማሻሻል የተከናወኑ የጥናት ሥራዎችም በሁሉም የግብርና ዘርፍ የምርት ዕድገትን በማስገኘት ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለምርት ዕድገት ገንቢ ሚና የሚጫወት የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂክ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።
የግብርና ሥርዓቱን ለማሻሻል የተከናወኑ የጥናት ሥራዎችም ለስትራቴጂክ ዕቅድና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት የግብርና ምርታማነትን እያሻሻለ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ዕድገትም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የአርሶ አደሮችን የግብርና ምርት ኮሜርሻላይዜሽን በማፋጠን ወሳኝ መሠረት እየተጣለ መሆኑን አንስተዋል።
የግብርና ማሻሻያ መርሃ ግብሮችም የአርሶና አርብቶ አደሮችን የሰብልና የእንስሳት የምርት ውጤቶች በብዛትና በጥራት የማምረት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአርሶ አደሮች በእጥፍ የማምረት አቅም መፈጠሩም በስንዴና በሩዝ ምርት ከኢትዮጵያ አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ተግባር በጥሩ ሁኔታ እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጉባ ብስራት ከሆኑት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ሲጠናቀቅም ከውጭ የሚገባን ግብዓት ለመተካት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አንስተዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካውም የግብርና ምርታማነትን የበለጠ ለማሻሻል ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።