ቀጥታ፡

በምስራቅ ቦረና ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

ነገሌ ቦረና፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ቦረና ዞን በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ ነው።

ምስራቅ ቦረና በአብዛኛው የእንስሳት እርባታ የሚካሄድበት ቆላማ፣ ዝናብ አጠር እና ደረቃማ ዞን እንደሆነ ይታወቃል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን መትከል፣ የውሃ አማራጮችን ለይቶ መጠቀምና ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን መስኖን ማስፋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግስት እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል ይጠቀሳል።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኩልሌ ሸና ፤በዞኑ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አዳጋዎች ሳቢያ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት እያስቻለ ነው ብለዋል።


 

በዘንድሮው ዓመትም በ6 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያላቸው  ችግኞችን  ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለመጪው ክረምት በዞኑ በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች የደን፣ የጥላ ዛፍ ፣ የእንስሳት መኖና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ሰፊ ስራ ተሰርቷል ያሉት ምክትል ኃላፊው በዚህም አብዛኛው ችግኝ መጽደቁን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተተከሉ  የጽድ፣ ግራቪሊያ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ የእንስሳት መኖ  እና የደንና የጥላ ዛፎች  በተሻለ ሁኔታ መጽደቃቸውንም ለአብነት አንስተዋል።

በዞኑ ሊበን ወረዳ የጎቢቻ ነዋሪ ሀጂ ቀራርሳ ጉራቻ፤ ባለፉት አመታት  በደኖች ላይ በደረሰ ጉዳት ድርቅና የአካባቢ መራቆት ሲያስከትል መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያዩ ችግኞችን በመትከል የተፈጥሮ ሀብቱን መልሶ ለመተካት እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር ችግኞቹን መትከልና መንከባከብ ለተሻለ ውጤት እንደሚያበቃ ነው የጠቀሱት።


 

አቶ አብዲ ሮባ የዚሁ ወረዳና ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በየአመቱ በአካባቢው በሚከሰተው  ድርቅ የወንዞችና ምንጮች መድረቅ፤ የእንስሳት መኖና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይ ችግር እንደሚያጋጥም ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተግባራዊ በተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ማህበረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ለመያዝ መቻሉንና ለውጥ መመዝገቡን ነው የገለጹት።

በዚህም ማሕበረሰቡ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ  እንክብካቤም እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመትም በተመሳሳይ መልኩ በመርሃ ግብሩ በመሳተፍ ዘላቂ ልማትና የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ የማተኮር እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በምስራቅ ቦረና ዞን በ9 ወረዳዎች ባለፈው አመት በአረንጓዴ አሻራ ከተተከለው ችግኝ ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ መጽደቁን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም