በምርጫ ወቅት ለሚነሱ ቅሬታዎች በሕግ ላይ የተመሠረተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ ወቅት ለሚነሱ ቅሬታዎች በሕግ ላይ የተመሠረተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018(ኢዜአ)፦ በምርጫ ወቅት ለሚነሱ ቅሬታዎች በሕግ ላይ የተመሠረተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት አስታወቁ።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር፣ በምርጫ ጉዳዮች ቅሬታ አፈታት ዙሪያ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ስልጠና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን፣ በምርጫ ቦርድ ባለሙያዎች እና በሰበር ሰሚ ዳኞች የሚሰጥ ሲሆን በሶስት ዙር 150 ዳኞች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
በዚሁ ጊዜ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፤ ዳኞች የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ጥራት በማሻሻል ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በምርጫ ሂደት ለሚነሱ ቅሬታዎች አፋጣኝ የፍትሕ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓትን በመፍጠር በኩልም ዳኞች ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል።
ምርጫ ዜጎች የሚመራቸውን አካል የሚመርጡበት ታላቅ ሀገራዊ ሂደት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሂደቱ ፍትሃዊ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በቀጣይ በምርጫ ሂደት የሚነሱ ቅሬታዎችን በሕግ ላይ የተመሰረተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ነው ፕሬዚዳንቱ ያረጋገጡት።
ለዚህም ዳኞች ለምርጫው ስኬታማነት የሚኖራቸውን ድርሻ ለማላቅ ሂደቱን ማስገንዘብ የሚያስችል ስልጠና መስጠት እንዳስፈለገ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በበኩላቸው፤ ቦርዱ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምርጫው ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተቀመጡ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ በቂ ግንዛቤ መያዝ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም በቅሬታ አቅራቢና በቅሬታ ፈቺ አካላት መካከል ወጥ የሆነ መረዳት ለመፍጠር ስልጠናው ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።