ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውድድር ለማድረግ የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት እያደረጉ ነው

ሀዋሳ፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውድድር ለማድረግ የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገለጹ።

በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው። 

በምርጫው ዝግጅት ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ፍትሀዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም በአሁኑ ወቅት በምርጫው ለሚወዳደሩ እጩዎቻቸውና አባሎቻቸው ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት። 

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሲዳማ አንድነት ፓርቲ (ሲአፓ) ሊቀ መንበር አቶ ለማ ሆያቶ፤ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ በዲጂታል ሥርዐት እንዲከናወን ማድረጉ እንግልትን ያስቀረና የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የምርጫው ሂደት ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ እንዲሆን ፓርቲው የሚጠበቅበትን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

አባላቶቻቸውና ዕጩዎቻችው ዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ የምርጫ ሂደትን ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ ግንዛቤያቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለሰላምና ትብብር ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በደቡብ ቀጠና ሲዳማ ክልል ማስተባበሪያ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሀረገወይን ዘሪሁን፤ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በምርጫው ለመሳተፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።  

በአሁኑ ወቅትም እስከ ታችኛው መዋቅር በመውረድ የዕጩ ምልመላ፣ የዕጩዎች ምዝገባና ሌሎች ሥራዎችን ያለተግዳሮት በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ምርጫው የዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ የሚጠናከርበት መሆኑን ገልጸው፣ በአሁን ወቅት ዕጩዎቻቸው የምርጫን መሠረታዊ ዓላማዎች ተረድተው እንዲንቀሳቀሱ የማስገንዘብ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ኤርሚያስ፤ ለምርጫው አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምርጫው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሠላማዊና በሁሉም ዘንድ ቅቡልነት ያለው እንዲሆን አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያስታወቁት። 


 

በክልሉ በሁሉም የምርጫ ክልሎችና የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲወዳደሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ የሲዳማ ክልል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የፓርቲዎችና የመንግስት ግንኙነት ጤናማ እንዲሆንና ቅራኔዎች ሲኖሩም ፈጥነው እንዲፈቱ እየተጫወተ ያለው ሚና የላቀ ነው።

በዞንና በወረዳ ደረጃም የጋራ ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ በማድረግ ፓርቲዎች ለምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊነት በጋራ የሚመክሩበትና ችግሮችን የሚፈቱበት መድረክ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም