ቀጥታ፡

ዘጠነኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2018 (ኢዜአ):- ዘጠነኛው የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሴኤ) ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሁነቱን አዘጋጅተውታል።

“የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ በፋይናንስ መደገፍ፤ ሥራ እና ኢኖቬሽን ለዘላቂ ትራንስፎርሜሽን” የፎረሙ መሪ ሐሳብ ነው።

የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ የልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄድ ከፍተኛ አኅጉራዊ የምክክር መድረክ መሆኑን ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

አኅጉራዊው መድረክ የአፍሪካ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያንና የልማት አጋሮችን በአንድ መድረክ ያገናኛል።

ፎረሙ አጋርነትና የኢንቨስትመንት መጠንን ማሳደግ በተለይም የመንግሥት እና የግል የተቀናጀ የፋይናንስ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይወያያል።

የሥራ ዕድል፣ ምቹ የኢኖቬሽን ሥነ-ምኅዳር እና የአፍሪካን የፈጠራ ዐቅም አሟጦ መጠቀም በፎረሙ ላይ ምክክር ከሚካሄድባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በተለይም የዲጂታል ኢንዱስትሪዎች፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም እየሰፋ ያለው የአፍሪካ የፈጠራ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በፎረሙ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችና ማዕቀፎች ይተዋወቃሉ።

የወጣቶችን የኢኖቬሽን ሥራ ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር የሚያስተሣሥር የአፍሪካ የወጣቶች አይበገሬነትና ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ ይፋ ይሆናል።

በኢሲኤ የበለጸገውና የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ቃል ኪዳኖችን ትግበራ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ሥርዓትም በፎረሙ ይፋ ሆኖ ወደ ትግበራ ይገባል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሁነት ላይ የአፍሪካ ሀገራት የመሪዎች የምክክር መድረኮችና የባለሙያዎች ውይይቶች ይደረጋሉ።

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና የፈጠራ ባለሙያዎችን ከባለሀብቶች እና ፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ ዐውደ-ርዕይም ይካሄዳል።

ሁነቶቹ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨበጡ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ለመቀየር አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።

የአፍሪካ ቢዝነስ ፎረም በዘላቂ ልማት ግቦችና በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ ስትራቴጂካዊ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝም በመረጃው ተመላክቷል።

የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች https://linktr.ee/ENADigitalክቷል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም