ቀጥታ፡

39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔና የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በስኬት ተጠናቀዋል -የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔና የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በስኬት መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደኅንነት የበለጠ በማጠናከር፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እጀባና አስተማማኝ ጥበቃ በማድረግ ጉባኤዎቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ ማስቻሉን ገልጿል።

መላው የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አመራርና አባላት የተሰጣቸውን ግዳጅ በጥብቅ ዲሲፕሊን ለአፍታም ሳይዘናጉ 24/7 ሰርተው በመወጣታቸው እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ተባብረው በመሥራት እንዲሁም የትራፊክ መጨናነቅ በሚያጋጥምበት ወቅት በትዕግስት ጠብቆ እንግዶችን በማሳለፍ ላደረጉት ቀና ትብብር የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ምስጋና አቅርቧል፡፡

በመጨረሻም ፀጥታና ደኅንነት የማስከበር ሥራው እንግዶቻችን ወደ የሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም