በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል
ባህር ዳር፣የካቲት 8/2018(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
በባህር ዳር ከተማ “ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት” በሚል መሪ ሃሳብ ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛር ማጠናቀቂያ የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ በማጠናቀቂያ ውይይቱ ላይ እንደገለጹት ንቅናቄው የክልሉን ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያሳደገ መጥቷል።
ይህም የኢንዱስትሪዎችን የአሰራርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን በማዘመን ቀደም ሲል 46 በመቶ የነበረውን የማምረት አቅም ከ 62 በመቶ በላይ ማሳደጉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት፣ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዚህም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከክልሉ ጠቅላላ ምርት ያለው ድርሻ 10 ነጥብ 3 በመቶ እንዲሆን ማስቻሉን አመልክተዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክተል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው እንዳሉት የከተማውን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
ለአብነትም የኮሪደር ልማት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የአስፋልት መንገዶች፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የስማርት ሲቲ ትግበራና ሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ለኢንዱስትሪ ልማት የሚውል መሬት በማዘጋጀትና ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱን አንስተዋል።
ለዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ግልጽና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ለባለሃብቱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ አምራችና ሸማቹን ህብረተሰብ በቀጥታ ለማገናኘት እድል የፈጠረ እንደነበር የገለጸው ደግሞ የዳንኤልና ሙሉ ባልትና ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ዳንኤል አብረሃም ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ተደራጅተው ወደ ስራ ለሚገቡ ወጣቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁሞ በቀጣይም እንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽን የማዘጋጀት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክቷል።