አፍሪካ ወደ አስተማማኝ ሰላም፣ አህጉራዊ ትስስርና የጋራ ብልፅግና በቆራጥነት እየተራመደች ነው-የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ ወደ አስተማማኝ ሰላም፣ አህጉራዊ ትስስርና የጋራ ብልፅግና በቆራጥነት እየተራመደች ነው-የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2018 (ኢዜአ)፦አፍሪካ ወደ አስተማማኝ ሰላም፣ አህጉራዊ ትስስርና የጋራ ብልፅግና በቆራጥነት እየተራመደች መሆኑን የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበርና የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ገለጹ፡፡
39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ዛሬ በስኬት ተጠናቋል።
የህብረቱ ሊቀ-መንበርና የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ የጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በጉባኤው የጋራ አቋም የተንጸባረቀባቸው አጀንዳዎች ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ተናግረዋል።
እነዚህ ውሳኔዎች ወደ ተግባር ተተርጉመው የአፍሪካን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ጉባኤው በደማቅና በስኬታማ መንገድ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦና ላበረከቱት ምቹ የአቀባበል መስተንግዶ ምስጋና አቅርበዋል።
ሊቀመንበሩ አፍሪካ ወደ አስተማማኝ ሰላም፣ አህጉራዊ ትስስርና የጋራ ብልፅግና በቆራጥነት እየተራመደች መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ውክልና ለማሳደግ እና የውስጥ አቅምን ለማጠናከር የሚያስችሉ ቁልፍ ስራዎች እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የሚጋፈጧቸውን ተግዳሮቶች በመጥቀስ የአፍሪካ የሰላምና የደህንነት መዋቅሮች ይበልጥ ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይበልጥ ቀልጣፋ፣ በሰው-ተኮር ልማት ላይ ያተኮረ እና የአፍሪካውያንን ፍላጎት የሚያሟላ ጠንካራ ህብረት ለመገንባት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
በተለይ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረኮችና ተቋማት ውስጥ ያላትን ድምፅ ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ትግበራ ማፋጠን፣ በመሰረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና በሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የህብረቱ ሊቀመንበር አክለውም አፍሪካ በቡድን 20 መድረክ ላይ ያላትን ተሳትፎ በማስተባበር የጋራ ጥቅሟን ማስጠበቅ እንዳለባት አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን መቋቋም፣ የዲጂታል እና የመረጃ ሽግግር ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ለአህጉራዊ ዘላቂ ሰላም፣ ለውህደት እና ለጋራ ብልፅግና በጋራ እንቆማለን ብለዋል።