አፍሪካ የራሷን የክትባት እና የሕክምና ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለማምረት የሚያስችላትን ጉዞ መጀመሯ ወሳኝ እርምጃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ የራሷን የክትባት እና የሕክምና ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለማምረት የሚያስችላትን ጉዞ መጀመሯ ወሳኝ እርምጃ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2018 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ የራሷን የክትባት እና የሕክምና ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለማምረት የሚያስችላትን ጉዞ መጀመሯ ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከ39ኛ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን አፍሪካ በክትባት እና በሕክምና ምርምር ራሷን እንድትችል ለማድረግ ያለመ አቺቭ አፍሪካ (ACHIEVE Africa) የተሰኘ መርሐግብር ይፋ ተደርጓል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማትና የቁጥጥር ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) የዓለም ጤና ድርጅትን የደረጃ ሶስት ዕውቅና ማግኘቱ ትልቅ ስኬት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ዕውቅናው በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉት ጠቅሰው፤ የሀገሪቱ የቁጥጥር ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተአማኒነት እንዲኖረው እንደሚያደረግም ተናግረዋል፡፡
በአገር ውስጥ የሚመረት መድኃኒትና ክትባት ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በቀላሉ እንዲላክ ትልቅ መንገድ እንደሚከፍት ገልጸው፤ በግንባታ ላይ ያሉ የክትባት ፋብሪካዎች ስራ ሲጀምሩ ምርቶቻቸው ተቀባይነት እንዲያገኙ ያስችላልም ብለዋል፡፡
መንግስት ለአገር ውስጥ አምራቾች የግዥ ቅድሚያ በመስጠትና ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን በማቅረብ የግል ዘርፉ በጤናው ኢንዱስትሪ ላይ እንዲሳተፍ እያደረገ መሆኑም ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡
የዛምቢያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ በበኩላቸው፤ አፍሪካ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የገጠማትን አስከፊ ተሞክሮ በማስታወስ፣ የራሷን የክትባት እና የህክምና ምርቶች በወቅቱና በበቂ ሁኔታ ለማምረት የሚያስችላትን ጉዞ መጀመሯ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው ሙሉ የማምረት አቅም ሲኖር ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካ የመድሐኒት እና የክትባት ምርት አለመመጣጠን መኖሩን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህን ለማሻሻል ይፋ የተደረገው አቺቭ አፍሪካ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ የክትባትና መድሐኒት የማምረት አነስተኛ ድርሻን እስከ 2040 ወደ 60 በመቶ ለማድረስ የተገባው ቃል ወደ ተግባር መለወጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህ ስኬት የአፍሪካ አገራት የተቀናጀ የህክምና ደንብ ሊኖራቸውና እንቅስቃሴው ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ጋር መተሳሰር እንዳለበት ገልጸዋል።
የአቺቭ አፍሪካ በዋናነት ትኩረት ከሚያደርግባቸው ዘርፎች መካከልም በጂኖሚክስ ምርምር እና በክትባት ንድፍ ላይ፣ እንደ ኤች.አይ.ቪ እና ኤምፖክስ ባሉ ተላላፊ በሽታዎች መከላከያ ላይ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡