በጤና፣ በትምህርትና በኢኮኖሚው ዘርፎች እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ የአፍሪካ ሴቶችን ዐቅም የበለጠ ማሳደግ ጠቃሚ ሚና አለው - ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው - ኢዜአ አማርኛ
በጤና፣ በትምህርትና በኢኮኖሚው ዘርፎች እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ የአፍሪካ ሴቶችን ዐቅም የበለጠ ማሳደግ ጠቃሚ ሚና አለው - ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2018 (ኢዜአ)፡- በጤና፣ በትምህርትና በኢኮኖሚው ዘርፎች እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ የአፍሪካ ሴቶችን ዐቅም የበለጠ ማሳደግ ጠቃሚ ሚና እንዳለው ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አስገነዘቡ።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በጾታ እኩልነት፣ በጤና እና በትምህርት መርሐ-ግብሮች፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ የአፍሪካ ሴቶችን ዐቅም የበለጠ ማሳደግ ጠቃሚ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
በተለይም ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ የማኅበራዊ ልማት ተግባራት፤ የሴቶችን ዐቅም የበለጠ ስለሚያጎለብቱ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በጽሕፈት ቤታችን ባለፉት ስድስት ዓመታት 37 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው የሴቶችን እና የሕጻናትን የትምህርት ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ ተሠርቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ለሴቶች የሞያና የንግድ ክኅሎት ሥልጠና፣ የመሥሪያ ቦታ፣ ግብዓትና የመነሻ ካፒታል በማመቻቸት፤ ሴቶች በገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ ተሠማርተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ እንዲቀይሩ አድርገናል ነው ያሉት።
ሴቶችን በየዘርፉ ማሳተፍም ሀገርን በሙሉ እንደ ማሳተፍ ይቆጠራል ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ሊሳካ የቻለውም በርካታ ሚሊየን ሴቶች በፈቃደኝነት ስለተሳተፉበት መሆኑን አመላክተዋል።
የአየር ንብረት መዛባትን ለመቋቋምም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ ችግሮችን ለመቅረፍ፤ ሴቶች ወሳኙን ቦታ የሚያገኙበትን ዐውድ መፍጠር አለብን ብለዋል በመልዕክታቸው።
ለዚህ ደግሞ እኛ ቀዳማዊ እመቤቶች ከፍ ያለ ኃላፊነት አለብን በማለት አስገንዝበዋል።