በሶማሌ ክልል የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ
ጅግጅጋ፤ የካቲት 8/2018 (ኢዜአ)፡- በሶማሌ ክልል ጃረር እና ቆረሀይ ዞኖች ድግ እና ኑስደሪቅ ከተሞች ከ380 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር ኢ/ር) በምረቃው ላይ እንደገለጹት፤ ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ ርቀው ለሚገኙ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል።
በድግ ከተማ የተገነባው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የ24 ሠዓት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ከ2 ሺህ በላይ አባዎራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በኑስደሪቅ ከተማ የተመረቀው የፀሐይ ኃይል ማመንጫም ለ900 አባዎራዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ከለውጡ ወዲህ መንግሥት በሰጠው ትኩረት በክልሉ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተጨማሪ 101 ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመድ ሹክሪ በበኩላቸው፤ የተመረቁት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያፋጥኑ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።