ቀጥታ፡

የተፋሰስ ልማት ሥራው አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በእርሻ ዘርፍ እንዲሰማራ ያግዛል

ሠመራ፤ የካቲት 8/2018 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በእርሻ ዘርፍም እንዲሰማራ ያግዛል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።

የአፋር ክልል የ2018ዓ.ም የተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር "የተቀናጀ ማኅበረሰብ አቀፍ የተፋሰስ ልማት ለምግብ ሉዓላዊነነት ስኬት" በሚል መሪ ሐሳብ በአውሲ ረሱ ዞን አደአር ወረዳ ተጀምሯል።


 

ርዕሰ መሥተዳድር አወል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ማጠናከር አርብቶ አደሩ ሕብረተሰባችን ከሚታወቅበት የኑሮ መሠረት ጎን ለጎን በእርሻ ሥራ እንዲሰማራ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።

የተፋሰስ ልማቱ በድርቅና ሌሎች አደጋዎች ምክንያት እየተመናመነ የመጣውን የተፈጥሮ ሀብት በመመለስ ሕብረተሰቡ የምግብ ሉዓላዊነቱን እንዲያረጋግጥና ከተረጂነት እንዲወጣ ያስችላል ብለዋል።


 

በተለይም የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙና ምርታማ እንዲሆኑ በማድረግ አርብቶ አደሩ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን የእርሻ ሥራውን በማሳደግ፤ ለእንስሳቱ መኖ፣ ለራሱም የምግብ ፍጆታውን እንዲሸፍን የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ200 ሺህ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ ከ52 ሺህ ሔክታር በላይ የተፋሰስ ልማት ሥራ እንደሚከናወን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም