የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
“ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
ትናንት የተጀመረው ጉባኤ ዛሬም በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ መምከሩን ይቀጥላል።
ከመሪ ቃሉ ጋር በተያያዘ ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓት፣ አካታች እድገት፣ ጤናማ ማህበረሰብና ጠንካራ ስነ ምህዳር መገንባት፣ የተፈጥሮ ሀብት ዘላቂ አጠቃቀምና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ጉዳዮች ውይይት ይደረግባቸዋል።
ውሃ እና ንጽህና የአጀንዳ 2063 አጀንዳን ከማሳካት አንጻር ያላቸው ሚና ይቃኛል።
ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ ተቋማዊ እና የፋይናንስ ሪፎርሞች፣ ቀጣናዊ አጋርነትና አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላት ሚና ጉባኤው ከሚመክርባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
የአፍሪካ ህብረት የ2026 መሪ ሀሳብ ይፋ ማድረጊያ መርሐ-ግብርም ዛሬ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይገኝበታል። በመርሐ-ግብሩ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አመራሮች እና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ይገኛሉ።
የሀገራት መሪዎች የሚገኙበት የአፍሪካ ሀገራት የውሃ ኢንቨስትመንት እና ፋይናንስ የተመለከተ ከፍተኛ መድረክም ይካሄዳል።
የአፍሪካ ህብረት የደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ባለስልጠናት ኮሚቴ በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምክክር ያደርጋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሚገኙ የአፍሪካ አባል ሀገራት (A3) የሚኒስትሮች ስብሰባም ይከናወናል።
ሱማሊያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ላይቤሪያ የምክር ቤቱ የአፍሪካ አባል ናቸው።
የዓለም የጤና ስርዓት ምህዳርን ማሻሻል ላይ የዓለም ትብብር ምን መምሰል እንዳለበት የሚመክር ጉባኤም ይካሄዳል።
የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በአህጉሪቱ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ ላይ መግለጫ ይሰጣሉ።
በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የጎንዮሽ ሁነቶችም እንዲሁ ከዛሬ መርሃ ግብሮች መካከል ናቸው።
የተለያዩ የአፍሪካ ህብረት ተቋማት እና አደረጃጀቶች በስራዎቻቸው ዙሪያ መግለጫዎች እንደሚሰጡና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ውይይቶች እንደሚካሄዱ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።