ቀጥታ፡

ከሻዕቢያ መንግስት ጋር በማበር የሚመለስ የትግራይ ህዝብ ጥያቄ የለም - የትግራይ ተወላጆች

‎አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- ከሻዕቢያ መንግስት ጋር በማበር የሚመለስ አንዳች የሰላምና የልማት ጥያቄ የለም ሲሉ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ፡፡

ለትግራይ ክልል ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሻዕቢያ በላይ ጠላት የለም በማለት ነው የገለጹት።

የፌዴራል መንግስት በህገ መንግስቱና በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በትግራይ ክልል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ ነውም ብለዋል።


 

የትግራይ ለውጥ ፈላጊዎች ንቅናቄ "ሰላም ለህዝባችን፣ ለውጥ ለወደፊት ተስፋችን” በሚል መሪ ሃሳብ ከክልሉ ተወላጆች ጋር በአዲስ አበባ ምክክር አድርጓል፡፡

የትግራይ የለውጥ ፈላጊዎች ንቅናቄ አባልና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ አሰፋ አብርሃ በዚህ ወቅት፤ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመፍታት የተፈረመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በአግባቡ ተፈጻሚ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም ጥቂት የቀድሞ ህወሓት አንጃዎች የኢትዮጵያና የትግራይ ህዝብ ጠላት ከሆነው የሻዕቢያ መንግስት ጋር ተሰልፈው የኢፌዴሪ ህገ መንግስትና የፕሪቶሪያን ስምምነት መጣሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ለትግራይ ክልል ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሻዕቢያ በላይ ጠላት የለም ያሉት አቶ አሰፋ፤ ከሻዕቢያ ኃይል ጋር መሰለፍ ባንዳነት መሆኑን አስረድተዋል።

የትግራይ ህዝብ ከሁለተኛ ጥፋት ለመዳን ጦርነትን በመቃወምና በሰላማዊ መንገድ በመታገል ከኋላቀሩ አንጃ መላቀቅ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ምርጫ ተካሂዶ መደበኛና ህጋዊ መንግስት እንዲኖር መስራት የንቅናቄያቸው ዓላማ መሆኑን በመጥቀስ፤ ከፌዴራል መንግስት ጋር አብሮ መስራት ሀገራዊ ግዴታችን ነው ብለዋል፡፡

የትግራይ የለውጥ ፈላጊዎች ንቅናቄ አባል ሌተናል ጀኔራል ፃድቃን ወልደትንሳኤ፤ የፌዴራል መንግስት ተፈናቃዮችን በመመለስ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንቅፋት ሆኖ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡

የትግራይ የፖለቲካ ችግሮች በሂደት እንዲፈቱና ቅድሚያ ለተፈናቃዮችና ሰብዓዊ ድጋፍ የሚል ስምምነት እንደነበርም አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የቀድሞ ህወሓት አንጃ የራሱን ፍላጎት ለማሳካት ተፈናቃዮችን እንዳይመለሱ በማድረግ የፖለቲካ መያዣ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት በህገ መንግስቱና በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በትግራይ ክልል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የቀድሞው ህወሓት ከሻዕቢያ መንግስትና ሌሎች ፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር በመቀናጀት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ጥሶ ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንም ሌተናል ጀኔራል ጻድቃን አንስተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ችግር የሚፈታው በሰላማዊ መንገድና ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከሻዕቢያ ጋር በመተባበርና በጦርነት የሚፈታም ሆነ የሚሳካ ጉዳይ እንደሌለ በመግለጽ፤ የትግራይ ህዝብ በየአካባቢው ተደራጅቶ ባንዳና ባዳን መታገል አለበት ብለዋል፡፡


 

የባይቶና ፓርቲ ሃላፊ ክብሮም በርኸ በበኩላቸው፤ የቀድሞ ህወሓት የትግራይን ህዝብ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ስቃዩን ለማብዛት ከሻዕቢያ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ አካላት ከውጭ ጠላት ጋር በማበር ጦርነትን ወደ ትግራይ ለመመለስ እየሞከሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህ አካሄድ አደገኛ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተከብሮ በትግራይ ክልል አዲስ ምርጫ መደረግ አለበት ያሉት ሃላፊው፤ ለዚህ ደግሞ የፌዴራል መንግስትና የትግራይ ህዝብ ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የቀድሞ ህወሓት ከጅምሩ የአስተዳደርና የፖለቲካ ችግር ያለበት፣ የትግራይን ሕዝብ የማይመጥንና ጥቅሙን አስከብሮ የማያውቅ ነው ያሉት የመድረኩ ተሳታፊ ሀጎስ አብርሃ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ መምህር ገብረኪሮስ ሀይሉ በበኩላቸው፤ የትግራይ ህዝብ የመጀመሪያ ጥያቄ ሰላም እና ልማት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ልጆቹ ወደ ልማት እንዲሰማሩና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጽኑ ፍላጎት አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም