ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የፓን አፍሪካኒዝም ሚናዋን የሚያጎሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የፓን አፍሪካኒዝም ሚናዋን የሚያጎሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የፓን አፍሪካኒዝም ሚናዋን የሚያጎሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር ፍራንቺስካ ቤሎቤ ገለጹ።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ኮሚሽነር ፍራንቺስካ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጀምሮ በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች።
የዓድዋ ድል ለአፍሪካ ነጻነት ምልክት መሆኑን ጠቁመው፤ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መሪ ሚናዋን ተጫውታለች ብለዋል።
በተለይም አፍሪካዊያን አንድ ሆነው የሚገጥማቸውን ፈተና በትብብር እንዲወጡ መሰረት የጣለ እንቅስቃሴ ማድረጓንም ጠቅሰዋል።
የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾች የህብረቱ መቀመጫ ኢትዮጵያ እንዲሆን መወሰናቸው ኢትዮጵያ ለተጫወተችው ሚና እውቅና የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
አፍሪካ እየተለወጠ ባለው ዓለም ድምጿን እና ጥቅሞቿን ለማስከበር በአንድ ላይ መቆም ይገባታል ያሉት ኮሚሽነር ፍራንቺስካ፤ መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በጋራ መቆም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው መስክ ተሻጋሪ የኢንዱስትሪ ሥርዓት እየገነባች መሆኑን ጠቁመው፤ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ ልማት ወሳኝ የሆኑ የውኃ እና ኢነርጂ አቅርቦት ላይ እያከናወነች ያለው ሥራ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
በተለይም የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሥራዎች ለቀጣናዊ ትስስር ጉልህ ፋይዳ አላቸው ያሉት ኮሚሽነር ፍራንቺስካ፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የፓን አፍሪካኒዝም ሚናዋን የሚያጎሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የቀድሞ ሊቀ መንበር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የሚታሰበውን ትብብርና ብልፅግና እውን ለማድረግ የአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለዚህ ደግሞ ትብብር እና እንደ አፍሪካ ማሰብ ይገባል ያሉት ዶክተር ኒኮሳዛና፤ የአፍሪካዊያን ኩራት ከሆነው የዓድዋ ድል በህብረት መሥራትን ልንማር ይገባል ብለዋል።