ቀጥታ፡

   የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ

በሙሴ መለሰ

የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ (Assembly of Heads of State and Government) የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ የፖሊሲ እና የውሳኔ ሰጪ አካል ነው።

ይህ አካል ከሁሉም አባል ሀገራት የተውጣጡ የመንግስታት ወይም የሀገራት መሪዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ የህብረቱን የጋራ ፖሊሲዎች የመቅረፅ እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የመወሰን ስልጣን ተሰጥቶታል። 

በአፍሪካ ህብረት ድረ-ገጽ ላይ በቀረበው መረጃ መሰረት፣ የጉባኤው ዋና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፦ 

የፖሊሲ አቅጣጫዎች፦ የህብረቱን የጋራ ፖሊሲዎች መወሰን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች መለየት እና ዓመታዊ የሥራ መርሐ-ግብሮችን ያጸድቃል።

ውሳኔ አሰጣጥ፦ በአህጉራዊ ሰላም፣ ጸጥታ እና ልማት ላይ የመጨረሻ ውሳኔዎችን ያሳልፋል።

ክትትልና ግምገማ፦ የህብረቱን ፖሊሲዎች እና ውሳኔዎች አፈጻጸም መከታተል፣ እንዲሁም አባል ሀገራት ግዴታቸውን መወጣታቸውን ያረጋግጣል።

ሹመቶች፦ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እና ኮሚሽነሮችን ይሾማል።

ጣልቃ ገብነት፦ በአባል ሀገራት ውስጥ የጦር ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት ወይም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ ጣልቃ የመግባት ውሳኔ ያሳልፋል።

ክትትልና ግምገማ: የህብረቱን አካላት እና የስራ አፈጻጸም ይገመግማል።

በጀት እና መዋቅር፦ የህብረቱን በጀት ማጽደቅ፣ እንዲሁም የኮሚሽኑን አደረጃጀት እና ደንቦችን መወሰን። 

 

የጉባኤው አወቃቀር እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት

አባልነት፦ ጉባኤው የሁሉንም 55 አባል ሀገራት መሪዎች ወይም ሕጋዊ ተወካዮቻቸውን ያቀፈ ነው።

የውሳኔ አሰጣጥ፦ ውሳኔዎች የሚሳለፉት በስምምነት (Consensus) ሲሆን፣ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ግን በሁለት ሦስተኛ (2/3) ድምፅ ይወሰናሉ።

የአሰራር ጉዳዮች ደግሞ በቀላል አብላጫ ድምፅ ይጸድቃሉ።

ምልዓተ ጉባኤ (Quorum)፦ ማንኛውንም ስብሰባ ለማካሄድ ቢያንስ ሁለት ሦስተኛው የአባል ሀገራት ተወካዮች መገኘት አለባቸው። 

 

የጉባኤው ቢሮ (Bureau)

ጉባኤው በየዓመቱ የሚመረጥ አንድ ሊቀመንበር እና ሌሎች አራት አባላት (ምክትል ሊቀመንበሮች) ያሉት ቢሮ አለው።

ይህ ቢሮ የአህጉሪቱን አምስቱንም ቀጣናዎች (ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብ እና መካከለኛ አፍሪካ) ተዋጽኦ የጠበቀ መሆን ይኖርበታል። 

 

የጉባኤው አሠራር እና መደበኛ ያልሆኑ ስብሰባዎች

መደበኛ ስብሰባ፦ ጉባኤው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል።

ልዩ ስብሰባ (Extraordinary Session)፦ ማንኛውም አባል ሀገር ጥያቄ አቅርቦ በሁለት ሦስተኛ አባል ሀገራት ድጋፍ ካገኘ በማንኛውም ጊዜ ልዩ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል።

ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ፦ ጉባኤው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በአባል ሀገራት ተፈጻሚ መሆናቸውን የመከታተል እና የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።

 

የህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር፦ መሐሙድ አሊ ዩሱፍ (ጅቡቲ) እ.አ.አ በየካቲት 2025 ተመርጠው በአሁኑ ወቅት የህብረቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎች የሚመራውን ኮሚሽን እየመሩ ይገኛሉ።

ምክትል ሊቀመንበር፦ አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ (አልጄሪያ) የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።

በተለያዩ ዘርፎች የሚሰሩ ስድስት ኮሚሽነሮች በህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ክንፍ በሆነው ኮሚሽን እየሰሩ ነው።

39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

ከፍተኛው የውሳኔ ሰጪ አካል የሆነው ጉባኤው በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም