ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሀገራት ለቅርሶች ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል - ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ማሪያ ኔቬስ

‎አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-የአፍሪካ ሀገራት ለቅርሶች ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የኬፕቨርዴ ፕሬዝዳንት እና የባህል ተፈጥሮ እና ቅርስ ሻምፒዮን ጆሴፍ ማሪያ ኔቬስ ገለጹ።

39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የኬፕቨርዴ ፕሬዝዳንት እና የባህል ተፈጥሮ እና ቅርስ ሻምፒዮን ጆሴፍ ማሪያ ኔቬስ በቅርስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ማምሻውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

‎በአፍሪካ እስካሁን ድረስ ያልታዩ ብዙ ቅርሶች መኖራቸውን ገልጸው፤ እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር እነዚህን ቅርሶች ወደ ብርሃን ማውጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

‎የቅርሶችን መመለስ እና የካሳ ሂደት የቅርስ አጀንዳ ማዕከላዊ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ ‎በህብረቱ በኩል ለጉዳዩ ትኩረት እንደተሰጠው አውስተዋል።

‎‎ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በቅርሶች መመለስ ረገድ መሻሻሎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ‎ሆኖም ግን አሁንም የካሳ እና የማካካሻ ፍትሕ እንደሚጎድለው አንስተዋል።

‎እነዚህ ቅርሶች ለልማት ጠቃሚ መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከማንነት አንጻርም እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረው፤ ቅርስ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለልማትም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ማሪያ ኔቬስ‎ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቅርሶችን በዩኔስኮ ማስመዝገቡን አስታውሰው፤ ‎ለዚህም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

‎ቅርሶችን የመጠበቅና አዳዲስ ቅርሶችን በመዝገቡ ላይ የመጨመር ሥራዎችን የአፍሪካ ሀገራት በአርአያነት ሊከተሉት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም