ቀጥታ፡

በክልሉ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል

ሆሳዕና፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑሪዬ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

በሀላባ ዞን ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ፣ የተንጠልጣይ ድልድይና የመስኖ አውታር ፕሮጀክት  ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑሪዬ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል፡፡

ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶችም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ምርትን ወደ ገበያ ለማቅረብ እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁም ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።


 

የአካባቢው ማህበረሰብ የፕሮጀክቶቹን ደህንነት በመጠበቅ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የክልሉ መስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ በበኩላቸው የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመስኖ አውታር የማስፋፋት ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

ዛሬ በሀላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የሲምቢጣ የመስኖ ፕሮጀክት 80 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል ሲሆን 320 አባወራዎችንና እማወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ውሃ፣ መስኖ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ  ኃላፊ ተወካይ ወይዘሮ አለይካ ሽኩር  በበኩላቸው፣ በሀላባ ዞን ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተገንብቶ ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የቁልቢ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።


 

ዛሬ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ፕሮጀክቶች የዞኑን እድገት ለማፋጠን የሚያግዙ መሆኑን የተናገሩት የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን ናቸው፡፡

በተለይም የመንገድ ፕሮጀክቱ ምርታማነትን ለማሳደግና ምርትን በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡


 

በሃላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ሲምቢጣ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ገረመው መሀመድ እንደገለፁት፤ የመስኖ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል።

ከዚህ ቀደም ንፁህ  የመጠጥ ውሃ  በአካባቢያቸው ባለመኖሩ ውኃ ፍለጋ ረጅም ርቀት  ይጓዙ እንደነበር የገለጹት ደግሞ በዚሁ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ ወሲላ ኢብራሂም ናቸው፡፡ 

ቀደም ሲል ከአንድ ሰዓት በላይ ተጉዘው ለመጠጥ የሚያገኙት ውሃ ንፅህናው ያልተጠበቀ በመሆኑ ለተለያየ የጤና እክል ሲዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው ውሃ ለረጅም ጊዜ ችግራቸው ምላሽ የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም