በአፍሪካ ቀጣናዊ የንግድ ሰንሰለትን በመገንባት የአህጉሪቷን የግብርና መዋቅር ለማዘመን ዕድል እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ቀጣናዊ የንግድ ሰንሰለትን በመገንባት የአህጉሪቷን የግብርና መዋቅር ለማዘመን ዕድል እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-በአፍሪካ ቀጣናዊ የንግድ ሰንሰለትን በመገንባት የአህጉሪቱን የግብርና መዋቅር ለማዘመን ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ገለጹ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና (AfCFTA) እና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (AGRA) በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የነፃ ንግድ ቀጣናው ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ እና የአግራ ፕሬዝዳንት አሊስ ሩህዌዝ ፈርመዋል።
አጋርነቱ ቀጣናዊ የንግድ ሰንሰለትን በመገንባት የአፍሪካን የግብርና መዋቅር ለማዘመን ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።
አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ እንደገለጹት፣ አፍሪካ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በምግብ ዋስትና እጥረት አጋጥሟታል።
አህጉሪቱ ጥራጥሬዎችን ጨምሮ በርካታ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ከውጭ የምታስገባ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህ አካሄድ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል።
ከስምምነቱ ዋና ዋና ዓላማዎች መካከልም የንግድ መሰናክሎችን ማስወገድ፣ ወጪን መቀነስ እንዲሁም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ቅንጅት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ የሚያደናቅፉ አሰራሮችን በማቃለል ምርቶች በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አፍሪካ ለምግብ ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ወጪ መቀነስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የአግራን ቴክኒካዊ ክህሎትና የፖሊሲ እውቀት ከነፃ ንግድ ቀጣናው የንግድ መሳሪያዎች ጋር በማጣመር ውጤት ማምጣት ይገባል ብለዋል።
ላለፉት ሦስት ዓመታት ሁለቱ ተቋማት በጋራ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ዛሬ ስምምነቱን ይፋ የማድረግ መርሃ ግብር መከናወኑን አብራርተዋል።
ስምምነቱ የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት የሚያስችል የሦስት ዓመት የሥራ እና የድርጊት መርሃ ግብርን የያዘ ነው ብለዋል።
የአግራ ፕሬዝዳንት አሊስ ሩህዌዝ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ በፖሊሲ ደረጃ የታለሙ ትልሞችን ወደ አነስተኛ አርሶ አደሮች በማውረድ ተግባራዊ ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸዋል።
ስምምነቱ በበርካታ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ጠቁመው፤ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የግብርና ሥርዓት መገንባት፣ የምግብ ሥርዓቱን ከድርቅና ከጎርፍ አደጋዎች መከላከል እንዲሁም የግብርና ማቀነባበሪያዎችን ከንግድ ሰንሰለቱ ጋር በማገናኘት ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
በስምምነቱ መርሐ ግብር የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ጥምረት (AGRA) የቦርድ ሊቀ መንበር የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተገኝተዋል።