የአፍሪካን የፋይናንስ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አህጉራዊ ተቋማትን ማጠናከር ይገባል - የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የፋይናንስ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አህጉራዊ ተቋማትን ማጠናከር ይገባል - የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካን የፋይናንስ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የአህጉሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ማጠናከር እንደሚገባ የጋና ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ሻምፒዮን ጆን ማሃማ ገለጹ።
ከ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን፣ "አጀንዳ 2063ን በገንዘብ ለመደገፍ የአፍሪካን የፋይናንስ መዋቅር ማጠናከር" በሚል መሪ ሃሳብ የአፍሪካ ባለብዙ ወገን የፋይናንስ ተቋማት ሕብረት የውይይትና የትብብር ስምምነት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
ፕሬዝዳንት ጆን ማሃማ በዚሁ ወቅት፤ የአፍሪካ የፋይናንስ ሉዓላዊነት በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆን አለበት ብለዋል።
የአፍሪካ የገንዘብ ተቋምን (AMI) እስከ መስከረም 2026 ዓ.ም ድረስ ወደ ሥራ ለማስገባት አባል ሀገራት ረቂቅ ሕጉን እንዲያጸድቁና ማዕከላዊ ባንኮች አስፈላጊውን በጀትና የሰው ኃይል እንዲመድቡ ኮሚሽኑ ከአፍሪካ ማዕከላዊ ባንኮች ማህበር ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ባንክን (AIB) ወደ ሥራ ለማስገባት ከ17 ዓመታት በፊት የቀረበው ምክረ ሃሳብ ተፈጻሚ እንዲሆንና አባል ሀገራት ስትራቴጂውን በማጽደቅ ለመሠረተ ልማት የሚሆን የፋይናንስ አቅም እንዲገነቡ አስገንዝበዋል፡፡
አፍሪካ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲሻሻል ከመጠየቋ በፊት ቀደም ብሎ የራሷን የውስጥ ተቋማት በማጠናከር የመደራደር አቅሟን ማሳደግ እንዳለባት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር ፍራንቺስካ ቻቹፕ ቤሎቤ በበኩላቸው፤ አህጉሪቱ ከዓለም አቀፍ ጫና ለመውጣት የራሷን የልማት አርክቴክቸር መቅረፅ እንዳለባት ገልጸዋል።
የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የአፍሪካ የባለብዙ ወገን ፋይናንስ ተቋማት ጥምረት (AMFI) ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳማይላ ዙባይሩ በበኩላቸው፤ አህጉሪቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ አለመጠቀሟን አንስተዋል፡፡
ከሀብት አጠቃቀም አንጻር የጡረታ ፈንድን ለተራ ግንባታዎች ከማዋል ይልቅ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎች ማዋል ይገባል ብለዋል።
የአህጉሪቱን ከፍተኛ የወርቅ ክምችት የገንዘብ አሃድን ለማጠናከርና ለብድር ዋስትናነት የመጠቀም ባህል ሊዳብር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ማዕድናት በጥሬው እየወጡ የሌሎችን ሀገራት ኢንዱስትሪ በዝቅተኛ ዋጋ የሚደጉሙበት አሰራር ሊቆም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ አቅም ያለው የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት ጥምረት (AMFI) ተበታትኖ የሚገኘውን አህጉራዊ የፋይናንስ ሥርዓት ወደ አንድ በማምጣት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት በመድረኩ ተመላክቷል።