የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ የተጣለበትን አህጉራዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ የአባል አገራት የፋይናንስ አስተዋጽኦ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ የተጣለበትን አህጉራዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ የአባል አገራት የፋይናንስ አስተዋጽኦ ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ (AMA) የተጣለበትን አህጉራዊ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ የአባል አገራት የፋይናንስ አስተዋጽኦ ሊጠናከር እንደሚገባ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደለሰ ሚሚ ዳርኮ ገለጹ።
ኤጀንሲው "ለከፍተኛ ጥራት የሕክምና ምርቶች እና ለአፍሪካ የጤና ደህንነት የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ ስምምነትን ማፋጠን" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደለሰ ሚሚ ዳርኮ በዚሁ ወቅት፤ ኤጀንሲው የአፍሪካ ዜጎች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጥራቱን የጠበቀና ውጤታማ የሕክምና ምርቶችን በወቅቱ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የመድኃኒት ቁጥጥር ደንቦችን በአህጉር ደረጃ ማቀናጀትና የቁጥጥር የመረጃ ቋቶችን እንደሚገነባ ጠቅሰው በአህጉሪቱ የመድኃኒት ማምረቻዎችን ማቋቋም እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ የፈጠራ ስራዎችን ያበረታታል ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው ወደ ሙሉ ሥራ እንዳይገባ የሕጋዊ ስምምነት መዘግየት እና የፋይናንስ እጥረት እንቅፋት እንደሆኑበት ጠቁመው ይህንንም መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው ሙሉ አህጉራዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ቢያንስ 35 አገራት ውሉን ማፅደቅ እንደሚኖርባቸው ጠቁመው እስካሁን ውሉን ያፀደቁት ግን 31 አገራት ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኤጀንሲው ስምምነት እንዲፋጠንና አስተማማኝ የፈንድ ምንጭ እንዲኖርም ጥሪ አቅርበዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የኤጀንሲው ልዩ መልዕክተኛ ሚሼል ሲዲቤ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ የአፍሪካን የጤና ዘርፍ የቁጥጥር ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲ (AMA) ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆንና የአህጉሪቱን የቁጥጥር ሥርዓት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያሸጋግር፣ አህጉራዊ ውሳኔዎችን በየሀገራቱ ሕግ ውስጥ ማካተት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመለወጥና ግልጽነት ያለው የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
ኤጀንሲው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ወረርሽኞችና ድንገተኛ የጤና እክሎች በሚከሰቱበት ወቅት፣ በአህጉራዊ ትብብር አማካኝነት ፈጣንና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።