ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ሥራዎች የተገልጋይን እርካታ መጨመር ተችሏል

አዳማ ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ሥራዎች የተገልጋይን እርካታ መጨመር መቻሉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ አስታወቁ።

እየተካሄደ በሚገኘው የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ፤ ለጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በየደረጃው አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ነው።

በተለይም አገልግሎቶችን ወደ ተጋልጋዩ ማህበረሰብ ለማቅረብ ይቻል ዘንድ አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ተዘርግቶ ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዚህም ከ7 ሺህ በላይ ቀበሌዎችን በማዋቀር 54 ሺህ አመራር እና ባለሙያ መመደቡን ጠቅሰው ምቹ የሥራ ቦታም ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በከተሞችም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ አገልግሎቶች በአንድ ቦታ በቴክኖሎጂ ታግዘው እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ቀድመው አገልግሎት መስጠት በጀመሩ አምስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪዎች አገልግሎት ማግኘታቸውንም አስረድተዋል።

እስካሁን በክልሉ በከተሞችም ሆነ በገጠር በተሰሩ ሥራዎች የተገልጋዩ እርካታ እየጨመረ መምጣቱን ማወቅ ተችሏል ሲሉም አቶ አወሉ አክለዋል።


 

በጨፌው የክልሉ መንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ ከፍያለው ተፈራ፣ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።

በተለይም የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ የክልሉ ህዝብ ከመንግስት ጋር በቅርበት በመስራቱ በርካታ ታጣቂዎች ወደ ሰላም መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

በጥፋት መንገድ ላይ የሚገኙ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ የክልሉ መንግስት አሁንም በትዕግስት እንደሚጠብቅ ገልጸው፣የመንግስትን የሰላም አማራጭ ወደጎን በማለት የህዝብ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይጠናከራል ብለዋል።

ህዝቡም የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የድርሻውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።


 

በተመሳሳይ ህገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድን ለመከላከል የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን እና የጨፌው አባላትም ጥረቱን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግስት ገንዘብ ቢሮ ሀላፊ አቶ ቶሎሳ ገደፋ፣ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቁ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችም ፍትሃዊነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም