ቀጥታ፡

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተልእኮውን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት እየፈፀመ ነው 

ጋምቤላ ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-በሀገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማእከላዊ እዝ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ ግዳጅና ተልእኮውን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት እየፈፀመ መሆኑን የእዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ በተለይም በምእራብ የሀገሪቷ ክፍሎችና በደቡብ ሱዳን ድንበር  አካባቢዎች የሀገርንና የዜጎችን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢዎች ሰላምና ጸጥታን ለማወክ ሙከራዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በአካባቢው የተሰማራው የዳሎል ማእከላዊ እዝ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በጥፋት እንቅስቃሴ ላይ በነበሩ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰዱን አንስተዋል።

በተለይም በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሁለቱ ሀገራት የጸጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል ብለዋል።

በጋምቤላም ይሁን በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢዎች አሁን ላይ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።

የዳሎል ማእከላዊ እዝ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተልእኮውን በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት እየፈፀመ መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጀነራሉ በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም