አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉ ተለዋዋጭ ፈተናዎችን በቆራጥነት፣ በፈጠራና በጽናት እየተወጣች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉ ተለዋዋጭ ፈተናዎችን በቆራጥነት፣ በፈጠራና በጽናት እየተወጣች ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉ ተለዋዋጭ ፈተናዎችን በቆራጥነት፣ በፈጠራና በጽናት እየተወጣች እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ፡፡
አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቢያንስ ሁለት ቋሚ የምክር ቤት መቀመጫዎች ሊሰጧት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቢያንስ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች ሊሰጣት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
አህጉሪቱ የዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ተቀባይ ብቻ ሳትሆን፣ የወቅቱን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ቀጥተኛ ውሳኔ ሰጪ መሆን እንዳለባትም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ አንጡራ ሀብቶች መበዝበዝ ማቆም እንዳለባቸው የጠቆሙት ዋና ጸሐፊው፤ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ ፍትሐዊ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
አሁን ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ለሀብታም ሀገራት ያደላና ለአፍሪካ ኢ-ፍትሐዊ መሆኑን ጠቁመው፣ የአህጉሪቱ የዕዳ ጫና እንዲቃለልና የልማት ባንኮች ብድር እንዲጨምሩ ጠይቀዋል።
በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በሳህልና በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመፍታት አፍሪካ መራሽ የሰላም ስራዎች በቋሚ በጀት ሊደገፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ምክንያት ባልሆነችበት ሁኔታ ከፍተኛውን ዋጋ እየከፈለች መሆኑን በማንሳት፣ የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉ ተለዋዋጭ ፈተናዎችን በቆራጥነት፣ በፈጠራና በጽናት እየተወጣች ትገኛለችም ብለዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት እና በአፍሪካ ሕብረት መካከል ያለው አጋርነት ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ በቀጣይም በሰላም፣ በዘላቂ ልማትና በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ያለው ስትራቴጂካዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።