ለወጣቶች የሥራ ዕድል በማስፋት ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ለወጣቶች የሥራ ዕድል በማስፋት ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ
ድሬዳዋ ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-ለወጣቶች የሥራ ዕድል በማስፋት ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ተናገሩ።
በድሬዳዋ በ"ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሀግብር" ሰልጥነው የሥራ ትስስር የተፈጠረላቸው ከ940 በላይ ወጣቶች ዛሬ ተመርቀዋል።
መርሃ ግብሩ በመንግስትና በዓለም ባንክ ድጋፍ በሀገሪቱ ባሉ 11 ከተሞች እየተተገበረ መሆኑም ተመላክቷል።
በምረቃው ላይ እንደተገለጸው በመርሃ ግብሩ ታቅፈው ስልጠና የሚያገኙ ወገኖች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያላገኙና ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 ዓመት የሆናቸው ወጣቶች ናቸው።
ወጣቶቹ የህይወት እና ተግባር ተኮር የክህሎት ስልጠናዎችን በመውሰድ ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በቋሚነት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋትና ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በ11 ከተሞች እየተተገበረ ባለው በዚህ መርሃ ግብርም ከ52 ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ነው የገለጹት።
በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ 2 ሺህ 800 በላይ ወጣቶች በመርሃ-ግብሩ ታቅፈው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ 97 በመቶ የሚሆኑት ሰልጣኞች ተግባራዊ ልምምድ ባደረጉባቸው ተቋማት ቋሚ የሥራ ዕድል አግኝተዋል ብለዋል።
ይህን መልካም ተግባር ለአብነት በመውሰድና በራስ አቅም በማስፋት የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በዘላቂነት የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የወጣቶችን የሥራ ዕድል ለማስፋትና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
ለዚህም በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሀግብር የተከናወኑ ተግባራት ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ በመርሃግብሩ ሰልጥነው ቋሚ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ራሳቸውንና አገራቸውን በመለወጥ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል ።
ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
በዕለቱ ለሰልጣኞች፣ ለተግባራዊ ልምምድ ላመቻቹና የሥራ ዕድል ለፈጠሩ ተቋማትና ፋብሪካዎች የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል።