ዩኒቨርሲቲው ተተኪው ትውልድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ክህሎት እንዲያሳድግ ሚናውን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ተተኪው ትውልድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ክህሎት እንዲያሳድግ ሚናውን እየተወጣ ነው
ሮቤ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተተኪው ትውልድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ክህሎት እንዲያሳድግ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ከሮቤ ከተማ የተለያዩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው ባለፉት አራት ወራት በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርት መስኮች ላሰለጠናቸው ተማሪዎች ዕውቅና ሰጥቷል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ተቋሙ የአካባቢውን ማህበረሰብ ፍላጎትና ችግር መሰረት ያደረጉ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እያከናወነ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ከስቴም ፓዎር ድርጅት ጋር በመተባበር ከዚህ በፊት የከፈተው ቤተ-ሙከራ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ዘርፎች የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት ሁነኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተደራጀው ቤተ-ሙከራ በተለይ በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግና በሂሳብ የትምህርት ዘርፎች በተግባር የተደገፈ ትምህርትን በማጠናከር ሀገራዊና አካባቢያዊ ችግሮችን የሚፈታ ትውልድ ለመፍጠር ዓላማ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በተለይ ማዕከሉ የአካባቢው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የቴክኖሎጂና የስራ ፈጠራ ዝንባሌ እንዲኖራቸውና ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ትምህርታቸውን የተከታተሉ ተማሪዎች በሀገር ደረጃ ዓምና በተደረገው የሳይንስ ፌር ውድድር ላይ በመሳተፍ በአንደኝነት በማጠናቀቅ ዕውቅናና ሽልማት ማግኘታቸውን በማሳያነት አስታውሰዋል።
እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ቤተ-ሙከራ ተተኪውን ትውልድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ክህሎት በማሳደግ ሀገሪቱ ያቀደችው የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያን ትልም እውን ለማድረግ አዎንታዊ ሚና እንዳለውም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።
ቤተ-ሙከራው የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምህንድስናና የሂሳብ ትምህርቶች የተግባር መለማመጃ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስቴም ፓዎር ማዕከል አስተባባሪ መምህር አብደላ አማን ናቸው።
የሳይንስ ቤተ-ሙከራው ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲያጎለብቱ የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው እውቅና ካገኙ ተማሪዎች መካከል የሮቤ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደገና አበባ፣ ከዩኒቨርሲቲው ማዕከል ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ዲጂታል ትምህርትን ለማሳለጥ የሚያግዝ መተግበርያ በማበልጸግ በሀገር ደረጃ ተሸላሚ መሆኑን ነው የገለጸው።
በዩኒቨርሲቲው የተሰጣት ተግባር ተኮር ሥልጠና ቀደም ሲል የነበራትን የሳይንስና ፈጠራ ቴክኖሎጂ ዝንባሌን ይበልጥ ለማጠናከር ረድቶኛል ያለችው ደግሞ የጋለማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳራ መሐመድቃዲ ናት።
በዩኒቨርሲቲው የተደራጀው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል የዛሬዎችን ጨምሮ 350 ተማሪዎችን በዘርፉ አሰልጥኖ እውቅና ሰጥቷል።