ቀጥታ፡

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር በላቀ ብቃት የሚጠብቁ ጀግኖች እያፈራ ነው 

ሀዋሳ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር በላቀ ብቃት የሚጠብቁ ጀግኖች እያፈራ ነው ሲሉ የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ።

የልዩ ዘመቻዎቸ ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት በሀዋሳ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።


 

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ሰራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ  የትኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል አኩሪ ገድል እያስመዘገበ ነው።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በ65 ዓመታት ጉዞው ሀገርን ከፍ የሚያደርጉና ዳር ድንበሯን የሚጠብቁ ጀግኖች አፍርቷል ነው ያሉት።

እነዚህ ጀግኖች የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ሀገርና ህዝብ የማይረሳው ታሪክ መጻፍ የቻሉ መሆናቸውን በማንሳት።

የዕዙ የምስረታ በዓል መከበር እነዚህ ጀግኖች እንዲታወሱና ትውልዱ ከሰራዊቱ የሀገር ፍቅር፣ ክብርና መስዋዕትነትን እንዲማር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሀገርንና ህዝብን ሁሌም በዝግጁነት የሚጠብቅ፣ የውጊያ ማርሽ ቀያሪና የመሬት ላይ ድሮን ነው ብለዋል።

አትሌቶችን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ የሚያጋጥመውን መሰናክል በአሸናፊነት በመወጣት ለሀገሩ ከፍታ ሊተጋ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፣ የሲዳማ ህዝብና የልዩ ዘመቻዎቸ ዕዝ ለ65 ዓመታት ጠንካራ ቁርኝትና አንድነት እንዳላቸው አንስተዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ  የትኛውንም የጠላት ሃይል በብቃት መመከት የሚችል ጠንካራ አቅም መገንባቱንም ተናግረዋል።

ዕዙ ለትውልዱ ኩራት፡ የሀገር ክብር ምልክት መሆኑንም አመልክተዋል።

በሩጫ ውድድሩ በወንዶች የግል ተወዳዳሪው አትሌት ቢንያም መላክ በሴቶች ደግሞ ውድነሽ አለሙ የአንደኝነት ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በሁለቱም ጾታዎች ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የወጡ አትሌቶች ከዕለቱ የክብር እንግዶች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም